Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በርካታ ቢሊየን ብር በመመደብ የነዳጅ አቅርቦትን አስቀጥሏል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በርካታ ቢሊየን ብር በመመደብ እና አመራጮችን ሁሉ አሟጦ በመጠቀም የነዳጅ አቅርቦትን አስቀጥሏል አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

የአገልግሎቱ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በርካታ ቢሊዮን ብሮችን በመመደብ እና አመራጮችን ሁሉ አሟጦ በመጠቀም የነዳጅ አቅርቦትን አስቀጥሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በመሠረታዊ ፍላጎቶቿን በራሷ የምታሟላ ሉዓላዊ ሀገር ለመፍጠር ፖሊስ ቀርጾ እየሠራ ይገኛል ። በተለይም ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ቀድሞ ወደ ሥራ መግባቱ በሀገር ላይ ይደርስ የነበረን የከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከሌሎች ሀገር አንጻር በከፍተኛ ደረጃ ማስቀረት ችሏል።

ምንም እንኳ ሙሉ ለሙሉ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ገና ሰፊ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ጥረት ቢጠይቅም ባለፉት ስምንት ዓመታት በታዳሽ የኃይል ዘርፍ አቅርቦት ላይ የተሠራዉ ሥራ ግን አሁን ያለውን ቀወስ ለመቋቋም በእጅጉ አግዟል፡፡ እንደሚታወቀዉ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚገኙ ናቸው፤ ከውኃ፣ ከነፋስ፣ ከፀሐይ፡፡

በቀጣይ ከተጨማሪ ታዳሽ ምንጮች ማለትም ከጂኦተርማል እና ከኑክሊየር ኃይል በማመንጨት የኢትዮጵያን ፍላጎት በአስተማማኝ ደረጃ ለማሟላት እየተሠራ ነው፡፡

የኃይል ምንጮቻችን ታዳሽ በማድረጋችን አሁን ካጋጠመዉ ዓለማቀፍ የነዳጅ እጥረትና የዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችል የነበረን የአገራችን አምራች ኢንዱስትሪዎች ጫና ማስቀረት ችለናል፡፡

መንግሥት ላለፉት ዓመታት ዜጎች የታዳሽ ሀይልን አማራጭ እንዲጠቀሙ የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓቶችን በመዘርጋት ተግባራዊ አድርጓል ። በዚህም የመንግሥትን አቅጣጫ በመቀበል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም የጀመሩ ዜጎች አሁን የችግሩ ሰለባ አይደሉም፡፡ ይህም ለዘገዩት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥና የሚያስቆጭ፣ ለመንግሥት በሚከተለዉ የፖሊሲ አቅጣጫ ትክክለኛነት የበለጠ በራስ መተማመን የሚፈጥር ነው፡፡ በዚህ ወቅት ከ140 ሺህ ያላነሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አሉ፤ በአጠረ ጊዜ ይህንን መጠን በብዙ እጥፍ ለማሳደግ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት የኃይል ሉዓላዊነትን በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ ተመሥርቶ ለማረጋገጥ በከፍተኛ ጥረት ላይ ነው፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦትን በእጅ አሳድጎታል፡፡ የነፋስ የኃይል ማመንጫዎችም በየጊዜዉ እየተመረቁ ወደ ሥራ መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በአፍሪካ ግዙፍ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ሶላር ፓኔሎችን የማምረት ዐቅም ተፈጥሯል፤ እየተፈጠረም ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎም በእጅጉ እየተበረታታ ነው፡፡ የነዳጅ ማጣሪያ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካዎች ግንባታም እየተፋጠነ ነው፡፡

በእነዚህ ኹሉ ጥረቶች መካከል አሁን ያጋጠመው ዓለማቀፍ ቀውስ በዜጎቻችን ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመጠበቅ ቀደም ሲል ሲደጉም ከነበረው በተጨማሪ በየወሩ 20 ቢሊዮን ብር በመደጎም እና የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የነዳጅ አቅርቦትን አስቀጥሏል።

በአረንጓዴ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫችን ችግሩን በዘላቂነት ከሕዝባችን ጋር እንደምንሻገረው ግን መንግሥት ያምናል፡፡ የመውጫ በሩ ከቅርብ ርቀት ይታያልና፡፡

Exit mobile version