Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አትሌቲኮ ማድሪድ ከአርሰናል – ተጠባቂው ጨዋታ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ዛሬ ምሽት ቀጥሎ ይደረጋል፡፡

ምሽት 4 ሰዓት ላይ አትሌቲኮ ማድሪድ በሪያድ ኤር ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም የእንግሊዙን ክለብ አርሰናል ያስተናግዳል፡፡

የዛሬ ምሽት ተጋጣሚዎቹ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን በታሪካቸው ማሳካት ያልቻሉ ቡድኖች ናቸው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ሦስት ጊዜ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆን የቻለው አትሌቲኮ ማድሪድ ወደ ፍጻሜ የሚያደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ይፋለማል፡፡

በአሰልጣኝ ዲያጎ ሲሞኒ የሚመራው አትሌቲኮ በሩብ ፍጻሜው ሌላኛውን የስፔን ክለብ ባርሴሎና በድምር ውጤት በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜው መብቃቱ ይታወሳል፡፡

በላሊጋው ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል አልባ ጉዞ በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ድል የተመለሰው አትሌቲኮ ማድሪድ አሸናፊነቱን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

በዚህ የውድድር ዓመት ለማድሪዱ ክለብ በሻምፒየንስ ሊግ 9 ግቦችን ያስቆጠረው አርጀንቲናዊው የፊት መስመር ተጫዋች ዩሊያን አልቫሬዝ በምሽቱ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

ግማሽ ፍጻሜ ውስጥ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ በኦፕታ ቅድመ ትንበያ መሰረት ለዋንጫው ዝቅተኛውን ግምት ያገኘው አትሌቲኮ ማድሪድ በመድረኩ ለአራተኛ ጊዜ ለፍጻሜ ለማለፍ ከመድፈኞቹ ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡

በዚሁ ቅድመ ትንበያ መሰረት ለዋንጫው በቀዳሚነት የተገመተው አርሰናል ወደ ፍጻሜው ለመጓዝ የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡

አርሰናል በታሪኩ አንድ ጊዜ ብቻ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ላይ የተገኘ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2006 በመድረኩ የፍጻሜ ጨዋታ በባርሴሎና ተሸንፎ ዋንጫውን ማጣቱ ይታወሳል፡፡

ባለፉት ሳምንታት የእንግሊዝ ካራባኦ ዋንጫን በማንቼስተር ሲቲ የተነጠቀውና ከኤፍ ኤ ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው የተሰናበተው የሰሜን ለንደኑ ክለብ በሻምፒየንስ ሊጉ የሚኖረው ቆይታ ይጠበቃል፡፡

የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ለማሳካት የሚያደርገውን ጉዞ ለማጠናከር የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡

መድፈኞቹ ባለፈው ዓመት በመድረኩ ሀያል የሆነውን ሪያል ማድሪድ አሸንፈው እስከ ግማሽ ፍጻሜ መጓዝ ቢችሉም በፒኤስጂ ተሸንፈው ለፍጻሜ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በዚህ የውድድር ዓመት በሩብ ፍጻሜው የፖርቹጋሉን ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን በድምር ውጤት በመርታት ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰ ሲሆን፥ እስከምን ድረስ ይጓዛል የሚለው ተጠባቂ ነው፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ በፕሪሚየር ሊጉ ወደ ድል የተመለሰው አርሰናል ድሉን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስበርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አርሰናል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ፥ አትሌቲኮ ማድሪድ በአንዱ ድል አድርጎ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

ቡድኖቹ በዚህ የወድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ በሊግ ቅርጽ በተደረገ ጨዋታ ተናገኝተው አርሰናል 4 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በሪያድ ኤር ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ምሽት 4 ሰዓት ላይ መደረግ የሚጀምረውን ጨዋታ የ43 ዓመቱ ኔዘርላንዳዊ ዳኛ ዳኒ ማኬሊ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version