Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባለፉት ስምንት ዓመታት የኢንዱስትሪ ሰላምን ለመፍጠር በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስምንት ዓመታት ሰው ተኮር በሆኑ የሪፎርም ስራዎች የኢንዱስትሪ ሰላምን ለመፍጠር በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገዋል አለ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፡፡
የሰራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ137ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ51ኛ ጊዜ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽንና ከኢትዮጵያ አሰሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የፊታችን አርብ ይከበራል።
ቀኑ “የሰራተኛ መብት መከበር ለኢንዱስትሪ ሰላም እና ለምርታማነት መሠረት ነው” በሚል መሪ ሐሳብ ነው የሚከበረው፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ ዓለም ዓቀፍ የሰራተኞች ቀንን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸው÷ በሀገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ሰራተኛው ያለውን ሚና እውቅና ለመስጠት ቀኑ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ሰው ተኮር በሆኑ የሪፎርም ስራዎች የኢንዱስትሪ ሰላምን ለመፍጠር በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው÷ ሰራተኞች ምቹ የሆነ የስራ አካባቢ ሊኖራቸው እንደሚገባ አንስተው ይህም የኢንዱስትሪ ሰላምን በማረጋገጥ ምርታማነትን ይጨምራል ብለዋል።
እኛ እንደ አሰሪ የምንፈልገው የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲኖር፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ ስራ እንዲፈጠር፣ የሰራተኞች መብት እንዲከበርና ክህሎት እንዲጨምር ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዳዊት ሞገስ (ዶ/ር) ናቸው።
የሰራተኞች መብት ሲከበር የስራ ከባቢ ሰላም ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።
በዘመን በየነ
Exit mobile version