አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ዙሪያ የኃይል ፍላጎት በየዓመቱ በ2 ነጥብ 2 በመቶ እያደገ ባለበት በዚህ ወቅት ሀገራት ፊታቸውን ወደ ታዳሽ ኃይል እያዞሩ ይገኛሉ።
በተለይም የሶላር ኃይል ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ የ70 በመቶ በላይ የዋጋ ቅናሽ በማሳየቱ ከዓለም አቀፉ የኃይል አቅርቦት ውስጥ ትልቁን ድርሻ እየያዘ መጥቷል።
በአሁኑ ወቅት ቻይና በዓለም ላይ ከሚመረቱ የሶላር ፓነሎች 80 በመቶ የሚሆነውን በማምረት ቀዳሚ መሆኗን መረጃዎች ያመላክታሉ፡
አህጉራችን አፍሪካ ደግሞ ከፍተኛውን የዓለም የፀሐይ ብርሃን ሃብት ድርሻ ብትይዝም እስካሁን የተጠቀመችው ግን ከ1 በመቶ በታች ነው።
ይህም እንደ አህጉር በዘርፉ ከተመልካችነት ያለፈ ሚና እንደሌለን የሚያሳይ እውነታ ሆኖ የቆየ ነበር።
አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ለአህጉርም የሚተርፍ የሶላር ኃይልን ማምረት በመጀመር ርምጃዎቿን አጠናክራለች።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመረቋቸው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙት የቶዮ ሶላር ኢነርጂ 2ኛው ምዕራፍ፣ ኦርጅን እና ሉሚንቴክ የሶላር ፋብሪካዎች እንዲሁም የኤች ዜድ ጋዝ ፋብሪካዎች ኢትዮጵያን በዚህ ዓለም አቀፍ ጉዞ ውስጥ አስገብተዋታል።
ይህም ኢትዮጵያ ከታሪክ ተመልካችነት ወደ ዋና አምራችነት እንድትሸጋገር ያስቻላት ሲሆን÷ በሀዋሳ የተመረቁት ፋብሪካዎችም በዓመት 11 ነጥብ 3 ጊጋ ዋት የሶላር ሃይል የማምረት አቅም አላቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በሀዋሳ ብቻ 15 ነጥብ 3 ጊጋዋት የሶላር ኃይል ፤ በአጠቃላይ እንደ ሀገር በቀጣዩ ዓመት ከ20 ነጥብ 3 ጊጋዋት በላይ የሶላር ሃይል ማምረት እንደሚቻል በወቅቱ አስገንዝበዋል።
ዘርፉ 1 ቢሊየን ዶላር በዓመት ለሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪን እንደሚያስገኝም ነው ያመላከቱት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ÷ አሁን ላይ የፀሐይ ብርሃንን ወደ ዶላር የመቀየር ሥራ ተጀምሯል ፤ ይህ ሥራም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሶላር መለዋወጫዎች ማዕከል ያደርጋታል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ የጨለማ ሳይሆን የብርሃንና የቴክኖሎጂ ምንጭ በማድረግ በታዳሽ ኃይል አጠቃቀም የአፍሪካ ታዳሽ ኃይል ማዕከል በማድረግ አህጉራዊ የኃይል ትስስርን የሚያጠናክርና ለጎረቤት ሀገራት አስተማማኝ የንጹህ ኢነርጂ አቅራቢ እንድትሆን የሚያስችል ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
በሶስና አለማየሁ

