አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ ከኢራን ጋር ባደረገችው ጦርነት እስካሁን 25 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማውጣቷ ተሰምቷል።
ሮይተርስ የአሜሪካ ወታደራዊ መስሪያ ቤት ፔንታገን ከፍተኛ ባለሥልጣንን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው አብዛኛው ወጪ የወጣው ለጦር መሣሪያ ነው።
ከሁለት ሳምንታት በፊት በወጣ መረጃ ኢራን በጦርነቱ 145 ቢሊየን ዶላር ማውጣቷ ተመላክቷል።
ጦርነቱ በተጀመረ በ6 ቀናት ብቻ የፔንታጎን ባለስልጣናት 11 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ወጪ መደረጉን መግለጻቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለመቋጨት ኢራን በቅርቡ ባቀረበችው የመደራደሪያ ነጥብ በተለይ የኢራን የኒውክሌር መርሐ ግብር ስምምነት እንዲዘገይ በሚጠይቀው የድርድር ነጥብ ላይ ደስተኛ አለመሆናቸው ታውቋል።
ይህም ጦርነቱ እንዲቋጭ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ እንቅፋት መሆኑ ተገልጿል።
ሁለት ወራት ገደማ ያስቆጠረው የአሜሪካ-እስራኤል እና ኢራን ጦርነት የኃይል አቅርቦት ያስተጓጎለ፣ የነዳጅ ዋጋ ያናረ እና የሺዎችን ሕይወት የቀጠፈው ሆኖ ዘልቋል።
በብርሃኑ አበራ

