አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካን የልማት አጀንዳ በማሳለጥ ረገድ እያሳዩት ያለው የአመራር ብቃት የሚደነቅ ነው አሉ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሃፊ ክላቨር ጋቴቴ፡፡
ዋና ፀሃፊው ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ የሰራችውን ሥራ አድንቀው፥ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ጉባኤ እንድታስተናግድ መመረጧ ትልቅ አህጉራዊ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተግባራትን ቀዳሚ ትኩረት ከሚሰጣቸው የልማት አጀንዳዎች ጋር በማጣጣም ያላት ስኬታማ ተሞክሮ ለዚህ ታሪካዊ ሚና ብቁ እንዳደረጋት አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ስኬቶች መካከልም ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በትልቅነቱ የሚጠቀሰው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአየር ንብረትና የዘላቂ ልማት ሥራዎች ለአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስ የሚደጋገፉ ተግባራት መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የአፍሪካ የልማት ጥረት በተቀዛቀዘው የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት፣ በፋይናንስ ጫና እና በጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ውስጥ እያለፈ መሆኑን ጠቅሰው፥ እነዚህ ተግዳሮቶች አህጉሪቱ የተለመቻቸውን ግቦች ሊገቱ እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ ቀጣናዊ ውህደቶችን ማጠናከር ለልማቱ ስኬት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል፡፡
በመሳፍንት ብርሌ

