አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ እንዳሉት÷ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አስገኝተዋል፡፡
የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በስኬት ለማጠናቀቅም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ለመርሐ ግብሩ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በዚህም የቡና፣ የፍራፍሬ፣ የጥምር ደን እና ሌሎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ከ1 ሚሊየን ሔክታር በበላይ መሬት መዘጋጀቱን አቶ በሪሶ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
ለተከላ የሚዘጋጁት ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን ጠቁመው ÷ ለዚህም የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለችግኝ መትከያ ቦታዎች የካርታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ከሚዘጋጁት ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኞች ውስጥ 4 ነጥብ 8 ቢሊየን የሚሆኑትን ለመትከል እንደሚሰራም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የታቀደውን ሥራ በስኬት ለማጠናቀቅ የክልሉ ሕዝብ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

