Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል ኢንዱስትሪዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በተቀናጀ ጥረት እየተፈቱ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በክልሉ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በተቀናጀ ጥረት እየተፈቱ ነው አሉ።

‘ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት’ በሚል መሪ ሀሳብ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ባለሀብቶች በተገኙበት በደብረ ብርሃን ከተማ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ እየተካሔደ ይገኛል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ምርታማነት ጨምሯል ብለዋል።

መሰረተ ልማትን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ጥያቄዎቹ እየተፈቱ ነው ብለዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተፈሪ ታረቀኝ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 137 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መግባታቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም ስራ አቁመው የነበሩ 46 መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን ገልጸው፤ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ካለፈው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ 2 ሺህ 946 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፤ ለ620 ባለሀብቶች መሬት መተላለፉን ገልጸዋል።

በታለ ማሞ

Exit mobile version