አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ጠንካራ አስተዳደር እና አመራር ያላቸው ተቋማት ስጋትን አስወግደው ተወዳዳሪነትን ይገነባሉ አሉ።
ካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል አ.ማ ያዘጋጀው የኮርፖሬት አስተዳደር እና አመራር ዙሪያ ላይ የሚመክር መድረክ የብሔራዊ ባንክ፣ የባንኮች እና የመድን ኩባንያዎች የቦርድ አመራሮች እና ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ የተቋማት ስኬት ለሀገር እድገት ቁልፍ ስለሆኑ ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል።
ተምሳሌት የምትሆን ሀገር ለመፍጠር የፋይናንሱን ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ በፋይናንስ ዘርፍ የተሰራው ሪፎርም ስር ነቀል ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።
መድረኩ የፋይናንስ ስርዓት መረጋጋት፣ ተወዳዳሪነት፣ ጤናማነት እና ውጤታማነት ላይ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
በብርሃኑ አበራ

