አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በየዓመቱ በፈረንጆቹ ግንቦት 1 ቀን (ሜይ ዴይ) ሲመጣ ዓለም የሰው ልጅ የጥረትና የትግል ውጤት የሆነውን የሰራተኞች ቀንን በድምቀት ታከብራለች።
ይህ ቀን ዝም ብሎ የመጣ የዕረፍት ቀን ሳይሆን በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰራተኞች ለክብራቸውና ለመብታቸው ያደረጉት ተጋድሎ መታሰቢያም ነው።
የዕለቱ ታሪክ የሚጀምረው በፈረንጆቹ 1886 በአሜሪካ ቺካጎ ከተማ በወቅቱ ሰራተኞች በቀን እስከ 16 ሰዓት ያለ ዕረፍት እንዲሠሩ በሚገደዱበት ወቅት ነበር።
ይህንንም ግፍ የተቃወሙ የቺካጎ ሰራተኞች “8 ሰዓት ለሥራ፣ 8 ሰዓት ለዕረፍት፣ 8 ሰዓት ለራሳችን” በሚል መሪ ቃል በሄይማርኬት አደባባይ ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው ዓለምን የሚቀይር አዲስ የሥራ ሕግ እንዲረቀቅ መሠረት ጣሉ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ የሰራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበር ጀመር።
በኢትዮጵያ ላለፉት 51 ዓመታት በየዓመቱ ሚያዚያ 23 (በፈረንጆቹ ግንቦት 1) የኢትዮጵያ ሰራተኞች የሀገር ግንባታ ምሰሶ መሆናቸውን በማስታወስ፣ የሰራተኛ ማኅበራት መብታቸውን የሚያስከብሩበትና ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ታላቅ ዕለት በማድረግ በዓሉ ሲከበር ቆይቷል።
ዛሬ ላይ ይህንን ዕለት ስናከብር ከታሪክ ባለፈ የነገውን ተስፋ እያለምን ነው።
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የምትሰራው በአባቶቻችን ደም ብቻ ሳይሆን በእኛም ላብ እንደሆነ አምነን እየሰራን ነው ሲሉ ሰራተኞች ለሀገር ግንባታ አበርክቷቸው የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል።
የነገዋ ኢትዮጵያ ከግዙፍ የኢንዱስትሪ መንደሮች እስከ ቴክኖሎጂ ተቋማት፣ ከግብርናው እስከ አገልግሎት ዘርፉ በአጠቃላይ በሰራተኛው ላብና ብልሃት ላይ እየተገነባች ነው።
የሰራተኝነት ትርጉሙ መሥራት ብቻ ሳይሆን ፈጠራና ጽናትም ጭምር ለመሆኑ ዛሬ የምንጠቀምባቸው መንገዶች፣ የምንኖርባቸው ሕንፃዎችና የምንመገበው እህል ሁሉ አመላካቾች ናቸው።
የዘንድሮ የሰራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ137ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ51ኛ ጊዜ “የሰራተኛ መብት መከበር ለኢንዱስትሪ ሰላም እና ለምርታማነት መሠረት ነው” በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል።
ቀኑ ሲከበር ሰራተኛውና አሰሪው እንዲሁም መንግሥት ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ መሆን የሚገባው ሲሆን፤ ሁሉም ወገን ያለበትን ክፍተት በማረም ትብብርን ለማጠናከር ቃል በመግባት ለተግባራዊ ምላሽ መነሳሳት አለበት።
በሶስና አለማየሁ

