አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ በመዲናዋ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሰው ተኮር ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
በተለይም የመኖሪያ ቤት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውሰዋል፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት ከተከናወኑ 60 ሺህ ፕሮጀክቶች መካከል ከፊሉ በሕዝብ ተሳትፎ የተከናወኑ ናቸው ያሉት ከንቲባዋ÷ሕዝቡ ላደረገው ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይ አዲስ አበባ ከተማ የደረሰችበትን ደረጃ የሚመጥኑ እና ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡
በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው ÷ ለዚህም ሕብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሕዝብ አምኖ ተጨማሪ 5 ዓመታትን በድምጹ ከሰጠን መዲናዋን ብሎም ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
‘ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር’ በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የቅስቀሳ መርሐ ግብር ከአዲስ አበባ ሁሉም ክ/ከተሞች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በመራኦል ከድር

