Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የብሔራዊ ሉዓላዊነታችን ማዕከል ነው – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የብሔራዊ ሉዓላዊነታችን ማዕከል ነው በሚል የመደመር መንግስት እሳቤ መሰረት በተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል አሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፡፡

4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል።

አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በኤክስፖው ላይ 370 አምራቾችና ከ150 ሺህ በላይ ጎብኚዎች እንደሚሳተፉና ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ግብይት እንደሚፈጸም ይጠበቃል፡፡

የቀረቡት ምርቶች ብዝሃነት፣ ጥራትና የሀገር በቀል ፈጠራዎች የደረሱበት ደረጃ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና የፈጠራ አቅም ብልጽግናዋን ማረጋገጥ እንደምትችል የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመደመር መንግስት እሳቤ በመነሳት ከለውጡ ወዲህ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ዘርፉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዚህ እሳቤ መሰረት ኢንዱስትሪ ለሀገር ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የሀገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅና ከጥገኝነት ተላቆ ራስን ከመቻል እንዲሁም ከሀገራዊ ክብር አንጻር እንደሚመለከተው ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን አምራች የሰው ኃይል ተጠቅማ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ረገድ እየታዩ ያሉ ተጨባጭ ውጤቶች ከብልጽግና ጉዟችን የሚያስቆመን ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመላ ሀገሪቱ 222 ኤግዚቢሽኖች ተዘጋጅተው ከ17 ሺህ በላይ አምራቾች ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ ችለዋል ያሉት ሚኒስትሩ፥ 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገደማ ግብይት መፈጸሙን አንስተዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version