Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አርበኝነት – ከትናንት እስከ ዛሬ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሚያዝያ 27 ኢትዮጵያውያን በታላቅ መስዋዕትነት ፋሺስት ጣሊያንን ድል አድርገው የአርበኝነት ዓርማቸውን ከፍ ያደረጉበት ታሪካዊ ቀን ነው።

የኢትዮጵያ አርበኝነት ልዩ የሚያደርገው “በየዘርፉ” የተደረገ ተጋድሎ በመሆኑ ነው።

በጊዜው በዱር በገደሉ የተዋጉ አርበኞች፣ በየከተማው መረጃ በማቀበልና የጠላትን እንቅስቃሴ በመሰለል ሕይወታቸውን የሰጡ የውስጥ አርበኞች እንዲሁም ስንቅና ትጥቅ በማቀበል የጀርባ አጥንት የሆኑ እናቶች ድሉን የጋራ አድርገውታል።

ይህ ተጋድሎ ኢትዮጵያዊነትን በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተስፋና ተምሳሌት ያደረገ ነው።

በዚህኛ ዘመን ደግሞ አርበኝነትን የምንለካው በጦር ሜዳ ጀግንነት ብቻ ሳይሆን ሀገርን በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ከፍ በሚያደርጉ የልማት ስኬቶች ነው።

በዚህም መንግሥት በየዘርፉ ያስመዘገባቸው ድሎች የዘመኑ የአርበኝነት ማሳያዎች የሚሆኑ ናቸው።

ለአብነትም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸው፣ አረንዴ ዐሻራ፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስሪ እና በቱሪዝም በአጠቃላይ በየዘርፉ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ይጠቀሳሉ።

እነዚህም ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ታላላቅ ሥራዎችን መሥራት እንደምትችል ለዓለም ያሳየችበት፣ የኢኮኖሚ ነጻነቷን ያረጋገጡና የአባቶችን ያለመሸነፍ መንፈስ በልማት የደገሙ ድሎቿ ናቸው።

በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየው የልመናና የጥገኝነት ታሪክ የቀየረው የክረምትና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ ሌላኛው የትውልዱ አርበኝነት ነው።

ይህ ስኬት ለዜጎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፣ ለውጭ ገበያ የሚተርፍ ምርት በማምረት ሀገራዊ ክብርን ከፍ አድርጓል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከልና የከተማ ገጽታን የሚቀይሩ የኮሪደር ልማቶች፣ ሀገርን ለትውልድ ምቹ የማድረግ አርበኝነት ነው።

እነዚህ ስኬቶች የዜጎችን የኑሮ ጥራት ከማሻሻላቸውም በላይ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተወዳዳሪነትና የቱሪዝም መስህብነት በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።

መንግሥት የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባትና ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓቶችን ለመዘርጋት እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች፣ ኢትዮጵያን ከዘመኑ ጋር የሚያሰልፉ ሌላኛው የዘመኑ የአርበኝነት ድሎች ናቸው።

ሀገራዊ ህልውናን ለማጽናት ልዩነቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ ከጥላቻ ንግግር መራቅና ለጋራ ሀገራዊ ጥቅም ቅድሚያ ለመስጠት የምክክር ኮሚሽን መቁቋሙም ሌላኛው የኢትዮጵያ ድል ነው።

በሶስና አለማየሁ

Exit mobile version