አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የጋራ ቴክኒካል ኮሚቴ ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው እንዲጠናከር የሚያስችል ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ እቅድ ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ከሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አስቀድሞ የሚከናወኑ የግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎችን ያመላከተ እቅድ ቀርቧል።
በውይይቱ የጋራ ቴክኒካል ኮሚቴው ሰብሳቢ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም÷ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአጋርነት ሳይሆን በባለቤትነት ስሜት ከኮሚሽኑ ጋር ለመስራት ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
ከዚህ በፊት ያሳዩትን አጋርነትና ሀገራዊ ሀላፊነት ለዋናው ጉባኤ መሳካትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ደገቲ÷ ምክር ቤቱ በምክክር ጉባኤው ከመሳተፍ ባሻገር ጉባኤውን በመታዘብና ለስኬታማነቱ የሚረዱ የተለያዩ ሰነዶችን በማዘጋጀት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
ከግንቦት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውን የምክክር ግንዛቤ ማስጨበጫ ዕቅድ ምክር ቤቱ ከኮሚሽኑ ጋር በቅንጅት በመሆን ተግባራዊ እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡

