አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ85ኛው የአርበኞች በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለ85ኛው የዐርበኞች (የድል) በዓል አደረሳችሁ!
ኢትዮጵያ ለዘመናት ታፍራና ተከብራ የኖረች፣ ሊወርሯት የሞከሩትን ያንበረከከች፣ የድል ታሪክ ባለ ሪከርድ ናት።
ይህም የሆነው ነጻነታቸውን በምንም የማይለውጡ፣ ለሀገራቸው ክብር ሕይወታቸውን የማይሰስቱ ጀግኖች ልጆች ስላሏት ነው።
ከዛሬ 85 ዓመት በፊት የጥንት ጀግኖች ዐርበኞቻችን ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አምስት ዓመታት ሙሉ በዱር በገደሉ ተጋድለው፣ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ሀገርን አጽንተው አቆይተውልናል። ዛሬ የምንተነፍሰው የነጻነት አየር የእነዚያ ታላላቅ ባለታሪኮች የጽናት ውጤት ነው።
ዐርበኞቻችን ታሪክ የሠሩት የውስጥ ባንዳንና የውጭ ባዳን ድል ነሥተው ነው። እኛም የአባቶቻችን ልጆች በመሆናችን አሁንም ያንን ድል እንደግመዋለን።
ዛሬ የዐርበኝነት ትርጉሙ ዘርፈ ብዙ ሆኗል። የዚህ ዘመን ዐርበኝነት በሥራ መትጋትና በዕውቀት መመራት፣ የድህነትን ታሪክ ለመቀየር ቆርጦ መነሣት፣ የተሻለች የነገዋ ኢትዮጵያን በላባችን መገንባት ነው።
ትውልዱ የአባቶቹንና የእናቶቹን ታሪክ ማድነቅ ብቻ ሳይሆን፣ የራሱን አዲስ ታሪክ መሥራት ይጠበቅበታል። አሁን በድህነትና በኋላ ቀርነት ላይ ዘምተናል፤ በሥራ ዐርበኝነትም ድል እያደረግናቸው ነው።
ስለሆነም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በዲፕሎማሲ መስኮች ድልን እያስቀጠልን፣ በተደመረ ዐቅም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ የሚያወጣ የዘመኑ ዐርበኛ ልንሆን ይገባል።
ኢትዮጵያውያን ዐርበኞች ሆይ! ስለ ሀገር አንድነትና ነጻነት ስለከፈላችሁት ውድ ዋጋ ዘላለም እናመሰግናለን!
ክብር ለጀግኖች ዐርበኞቻችን!

