አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአርበኞች ቀን በተለያዩ መስኮች የጀግንነት ሚና የተወጡ አርበኞቻችንን በማስታወስ እየዘከርናቸው ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ሀገር ለጠቢባን የሕያው ሥራዎቻቸው ምስክር ሐውልት ታቆማለች ብለዋል።
ሀገር በልማት ስራዎች፣ ድንበርን በመከላከል፣ በሰንደቅ ዓላማ እና በሕግ ብቻ አትገነባም ያሉት ከንቲባዋ÷ ሀገር የምትገነባው በሕዝብ የጋራ ትውስታ፣ በጋራ ስሜት እና በታላላቅ የጥበብ ውጤቶችም ጭምር መሆኗን አመልክተዋል።
ይህ እውነት ዛሬ በቆሙት የሀገር ባለውለታ ታላላቅ ጠቢባን ሐውልቶች በአዲስ አበባ ከተማችን እውን አድርገናል ሲሉም አስረድተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማት እና በታላላቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ ጥበብን ማዕከል ማድረጉንም ገልጸዋል።
ዛሬ ሐውልት የቆመላቸው ለሀገራቸው ሰላም፣ ለኢትዮጵያዊነት ግንባታ፣ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ ለወንድማማችነትና እህትማማችነት፣ ለፍትሃዊነት፣ ለነፃነትና እኩልነት ላቀነቀኑት አንጋፋዎቹ የሀገር ባለውለታዎች ሎሬት ጸጋዬ ጸጋዬ ጋብረ መድኅን፣ የክብር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ፣ ማሕሙድ አሕመድ፣ ዓሊ ቢራ፣ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር እና ሐጫሉ ሑንዴሣ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከእነዚህ በተጨማሪም ልናከብራቸው የሚገባን የሀገር ባለውለታዎች የሆኑ የጥበብ ሰዎች መኖራቸው ስለሚታወቅ ይህ ስራ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም ሲሉም አክለዋል።

