አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ትውልዱ ፈተናዎችን በጽናት ለመሻገር እንደ አባቶቹ የጸና አንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ሊኖረው ይገባል አሉ የባሕር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ።
85ኛው የአርበኞች በዓል በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሐውልት አደባባይ ተከብሯል።
የባሕር ኃይል አዛዡ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ወታደራዊ ጥበብ፣ በላቀ ሥነ ልቦና የታነጸና ጥቃትን በብቃት መመከት የሚችል ሠራዊት ገንብታለች።
ጀግንነት የኢትዮጵያውያን መታወቂያና የነፃነታቸው ዋስትና መሆኑን አንስተው÷ ሀገሪቱ በረጅም ዘመን ታሪኳ በልጆቿ መስዋዕትነት የነፃነትና የታላቅነት የድል ባለቤት መሆኗን አስረድተዋል።
የድል በዓሉ የአምስት ዓመታት የአርበኝነት ትግል ጊዜ አልፎ ዳግም የነፃነት ብርሃን የበራበት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በደማቅ ቀለም የተጻፈ ነው ብለዋል።
አርበኞች ወራሪ ኃይሉን መስዋዕትነት ከፍለው በትብብር ድል እንዳደረጉ ዛሬም ለሀገር ሕልውናና ሉዓላዊነት መከበር በአንድነትና በመተባበር ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በግፍ ያጣችውን የባሕር በር ለማስመለስ መንግሥት የሚያደርገውን ዘርፈ ብዙ ጥረት ለመደገፍ ጠንካራ የባሕር ኃይል እየተገነባ መሆኑንም ተናግረዋል።

