Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሰው ልጅ ቀደምት የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳዩ ቅሪተ-አካል መገኛ የሆነው መልካ ቁንጡሬ …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኘው መልካ ቁንጡሬ የሰው ልጅ ቀደምት የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳዩ ቅሪተ-አካል መገኛ ነው አሉ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር አበባው አያሌው።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ10ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ የአፍሪካ የዓለም ቅርስ ቀንን በመልካ ቁንጡሬ አርኪዮሎጂ ሳይት እያከበረ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የአርኪዮሎጂ ባለሙያዎች እና ባለድርሻዎች ተገኝተዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በወቅቱ እንዳሉት፥ መልካ ቁንጡሬ የሰው ልጅ ቀደምት የድንጋይ መሣሪያዎች አጠቃቀም እና የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳዩ በርካታ ቅሪተ-አካል መገኛ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ የዓለም ቅርስ ቀን መከበሩ ቅርሶችን ጠብቆ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል ያስችላል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ቅርሶችን ለትውልድ ለማቆየት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቀኑ መከበር ኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃና በቱሪዝም ዘርፍ እያከናወነች የምትገኘውን ተግባር ለዓለም ለማሳየት ይጠቅማል ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደራራ ከተማ ናቸው።
በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ቅርሶች እንዲተዋወቁና ከዘርፉ የሚገኘውንም ገቢ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በሰዓዳ ጌታቸው
Exit mobile version