Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባሕላዊ ስርዓት በአዲሱ የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍኤምሲ) ከ6ዐ ዓመታት በላይ ያገለገለውን የወንጀል ሕግ የሚተካ የወንጀል ሕግ ሥነ ስርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1410/2018 መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።

በአዋጁ የወንጀል ድርጊት በባሕላዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ የሚያስችል ዓላማ በመያዝ የባህላዊ ስርዓት ትግበራ በተጠናከረ መልኩ ተካትቷል።

ይህም በማኅበረሰቡ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ያስችላል።

በአዋጁ ማንኛውም በክስ እና የፍርድ ሂደት ላይ ያለ የግል ተበዳይ ያለበት የወንጀል ጉዳይ ማስረጃ ከመሠማቱ በፊት በባሕላዊ ሥርዐት መሠረት ታይቶ ውሳኔ ወይም መፍትሔ ሊሰጥበት ይችላል በሚል ተቀምጧል።

ሴትን መጥለፍ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ጨምሮ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ባሕላዊ ሥርዐት ተፈጻሚ እንደማይሆን የሚደነግገው አዋጁ፤ በዋናነት በባህላዊ ስርዓት የተከለከሉ ተግባራት በተሻሻለው ሕግ ላይ ተጠቅሷል።

ይህም ተከሳሹ በፈጸመው አንድ የወንጀል ጉዳይ ላይ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ባሕላዊ ስርዓቶችን ተፈፃሚ ማድረግ የተከለከለ ነው የሚል ይገኝበታል።

ሌላው ተከሳሹ ያልተቀበለውን ባሕላዊ ስርዓት ተፈጻሚ ማድረግ ወይም ባሕላዊ ስርዓቱን ከሌላ መፍትሔ ጋር መቀላቀል የተከለከለ ነው፡፡

በተጨማሪም ተከሳሹ ደተጋጋሚ ወንጀለኛ ከሆነ ጉዳዩ በባሕላዊ ስርዓት አይታይም፡፡

በዚህ ሕግ ለባህላዊ ስርዐት ተፈጻሚነት ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ሲሆን ፤ ይህም ለጉዳዩ እልባት የሚሰጥ የታወቀ ባህላዊ ስርዓት መኖሩ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ተደንግጓል።

ጉዳዩ በባህላዊ ስርዓት እንዲታይ በህጉ መሠረት ጥያቄ ሊቀርብ እንደሚገባ እና ተከሳሹ ጉዳዩ በባህላዊ ስርዓት ታይቶ እልባት እንዲያገኝ ፈቃደኛ ሊሆን ይገባል የሚል ይገኝበታል።

በተጨማሪም ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩ በባሕላዊ ሥርዐት እንዲታይ ሲወስን ተከሳሹን ጥፋተኛ ለማሰኘት የሚያስችል ማስረጃ መኖሩን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩ በባሕላዊ ሥርዐት እንዲታይ ውሳኔ ሲሰጥ እንደነገሩ ሁኔታ በጉዳዩ ላይ እውቀት ካለው ባለሙያ፤ ባሕላዊ ስርዓቱን ከሚያስፈፅሙ ሰዎች፣ ከተጎጂው ወይም ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት አስተያየት ሊጠይቅ ይችላል።

ሌላው ፍርድ ቤት በራሱ አነሳሽነት፣ በግል ተበዳይ በተከሳሽ ወይም በባሕላዊ ስርዓት ሥልጣን ባለው ሰው፣ አግባብ በሆነ የመንግስት አካል ወይም በዐቃቤ ሕግ አነሳሽነት የተፈጸመውን የወንጀል ድርጊት በባሕላዊ መንገድ እንዲታይ ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል፡፡

በተጨማሪም ፍርድቤቱ የዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሽን ፈቃደኝነት አረጋግጦ ጉዳዩን ወደ ባህላዊ ስርዓቱ ይመራዋል፡፡

የውሳኔ አሰጣጥን በሚመለከት ደግሞ የባህላዊ ስርዓቱ ጉዳዩን በ30 ቀናት አጠናቅቆ ውሳኔ ይሰጣል በሚል ተቀምጧል።

በባሕላዊ ስርዓት መሠረት የተሰጠ ውሳኔ ክሱ በተመሠረተበት ፍርድ ቤት የሥራ ቋንቋ ሆኖ በዐቃቤ ሕግ ወይም በአማራጭ ቅጣት አፈጻጸም ለቦርድ በጽሑፍ ይቀርባል፡፡

ፍርድ ቤት የቀረበው የባህላዊ ስርዓት ውሳኔ ሕግ እና ሞራልን የማይቃረን፣ ሰብዓዊ ክብርን የማይነካ መሆኑን፤ የሂደቱን ዓላማ ያሳካ መሆኑን በማረጋገጥ የሚያጸድቅ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ ያላፀደቀው ከሆነ የክስ ሂደቱ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡

በአዋጁ ላይ ተለዋጭ መፍትሔዎች የተቀመጡ ሲሆን፤ በዋናነት የወንጀል ጉዳይ በተለዋጭ መፍትሄዎች እልባት እንዲያገኝ የሚደረግበት ዓላማ የወንጀል ድርጊቱን ፈፅመዋል የተባሉ ሰዎች ከባሕሪያቸውና ከዕድሜያቸው ጋር በሚስማማ ሁኔታ እንዲያዙ፣ እንዲታከሙ ወይም ተገልለው እንዲቀመጡ በማድረግ የወንጀል ፍትህ ሂደቱን ፍትሐዊነትና ውጤታማነት ያረጋግጣል።

በዚህ መሰረት ተለዋጭ መፍትሔዎች ተፈፃሚ የሚሆኑባቸው ሰዎች በህጉ በዝርዝር ተቀምጧል።

ይህም ክስ በሚሰማበት ጊዜ አካላዊ ወይም አዕምሯዊ ሕመምተኛ ከሆነ የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል የማይችል ከሆነ፣ በዕድሜ ያረጀ (የጃጀ) ከሆነ፣ የአልኮል፣ የመድሐኒት ወይም የእፅ ሱሰኛ ከሆነ፣ ወይም ከአእምሮው ጤና መጓደል የተነሳ ወይም ሙያዊ ክህሎት በማነሱ ምክንያት ተደጋጋሚ ስህተት የሚሰራ ከሆነ ተለዋጭ መፍትሔዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ።

በተለየም ተከሳሹ በራሱ ወይም በመንግሥት ወጪ የሚሰጥ ሕክምና፣ የተሃድሶ ወይም የግብረ ገብ የሙያ ስልጠና፣ የቀለም፣ ትምህርት፣ ማሕበራዊ አገልግሎት መስጠት፣ ለተወሰነ ጊዜ በተወሰነ ቦታ መቆየት፣ ምክርና ተግሳጽ ወይም በሕግ የሚወሰነውን ሌላ አማራጭ መፍትሔን ሊያካትት ይችላል በሚል በአዋጁ ተካትቷል።

ክስ የተመሠረተበት ጉዳይ በዚህ መልኩ በተመላከቱ ተለዋጭ መፍትሄዎች መሠረት እልባት እንዲያገኝ በዐቃቤ ሕግ ወይም በተከሳሽ ጥያቄ ከቀረበ ወይም ፍርድ ቤት በራሱ አነሳሽነት ከወሰነ ፍርድ ቤቱ በተለዋጭ መፍትሄዎች እልባት እንዲያገኝ ለሚመለከተው ተቋም ይመራል፡፡

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version