አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አርቲስት ማህሙድ አሕመድ ለኢትዮጵያውያን “የትዝታ ንጉስ” ብቻ ሳይሆን የጽናት፣ የትህትና፣ የርህራሄ እና የጥበብ ተምሳሌት ጭምር ነው።
ማህሙድ አህመድ በ1933 ዓ.ም በአዲስ አበባ መርካቶ በተለምዶ አሜሪካን ግቢ በሚባለው አካባቢ ሲወለድ ህይወት አልጋ በአልጋ አልነበረችም።
ገና በልጅነቱ ኑሮን ለማሸነፍ በወቅቱ “ግሪክ ክለብ” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ጫማ በመጥረግና በረዳትነት በመስራት ነበር የልጅነት ጊዜውን የጀመረው።
የማህሙድ የሙዚቃ ህይወት የተጀመረው በአንድ አጋጣሚ “አሪዞና ክለብ” ውስጥ ሳንድዊች በማቅረብና በጽዳት ሰራተኛነት ይሰራ በነበረበት ወቅት ነው።
አንድ ምሽት የታዋቂው የክብር ዘበኛ ሙዚቀኞች ለመዝፈን ወደ ክለቡ ሳይመጡ ሲቀሩ በዚህ ወቅት ማህሙድ ወደ መድረክ ወጥቶ የመዝፈን ዕድል አገኘ።
ያቺ ምሽት የማህሙድን የህይወት መስመር የቀየረች እና ወደ ስድስት አስርት ዓመታት የጥበብ ጉዞ የመራች ታሪካዊ አጋጣሚ ሆነች።
ማህሙድ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ የኢትዮጵያ የሙዚቃ “ወርቃማ ዘመን” ውስጥ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው።
በርካታ ስራዎችን የሰራ ሲሆን “አልማዝ አየሁሽ”፣ “ትዝታ” እና “ኩሉን ማን ኳለሽ” “የሺ ሐረጊቱ” የሚሉት ስራዎቹ ትውልድ ተሻጋሪ ሆነዋል።
ከክቡር ዘበኛ፣ ከአይቤክስ፣ ቬነስ፣ ሮሃ፣ ዳህላክ፣ ዋልያስ እና ከራሱ የ3ኤም ባንዶች ጋር በርካታ መድረኮች ላይ ሰርቷል።
በ1990ዎቹ አጋማሽ “Éthiopiques” በተሰኘው የአውሮፓ የሙዚቃ ስብስብ ውስጥ ስራዎቹ መካተታቸው ደግሞ የአውሮፓ እና አሜሪካ ታዋቂ የሙዚቃ መድረኮች በክብር እንዲቀበሉት አድርጓቸዋል።
አርቲስት ማህሙድ አሕመድ በቅርቡ በይፋ ከሙዚቃ መድረክ ተሰናብቷል። ይህንኑ ስንብቱን አስመልክቶ የታላቅ የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ምረቃ እና የክብር ኮንሰርት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በኮንሰርቱ ላይ የታየው የህዝብ ፍቅር ማህሙድ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያለውን ቦታ በግልጽ ያሳየ ነበር።
በፈረንሳይ መንግስት “Officer of the Order of Arts and Letters” ተብሎ የተሸለመውና የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ይህ ታላቅ አርቲስት፣ ዛሬም ድረስ በባህር ማዶም ሆነ በሀገር ውስጥ ለሚነሱ ወጣት ድምጻውያን ትልቅ አርአያ ሆኖ ቀጥሏል።
በአሜሪካ አትላንታ ከተማ ውስጥ ኦገስት 18 ቀን የማህሙድ ቀን ተብሎ ተሰይሟል።
በ2007 የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ሙዚቃ ተሸላሚ መሆን የቻለ ሲሆን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶታል።
ማህሙድ ለኢትዮጵያ ሙዚቃና ባህል ላበረከተው የ63 ዓመታት ወደር የለሽ አስተዋፅኦ፣ በህይወት እያለ የሚገባውን ክብርና ዕውቅና ለመስጠት ያለመ የመታሰቢያ ሐውልት በአዲስ አበባ ተገንብቶ ይፋ ሆኗል።
በሶስና አለማየሁ

