Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሁለቱ የጥበብ ፈርጦች…

ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብላቴን ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን እና ደራሲ፣ አርታኢና ጋዜጠኛ ስብሐት ገ/እግዚአብሄር በሀገራችን ስነ ጽሁፍ ታሪክ ትልቅ ዝናን ያተረፉ አንጋፋ የስነ ጽሁፍ ሰዎች ናቸው፡፡

ሁለቱ የስነ ጽሁፍ ምልክቶች ዛሬ ላይ በህይወት ባይኖሩም በዘመን ተሻጋሪ ስራዎቻቸው በትውልድ የሚታወሱና ህያው ሆነው ዘልቀዋል፡፡

በአምቦ ከተማ አቅራቢያ ቦባዳ በተባለ ተራራማ ቦታ በ1928 ዓ.ም የተወለደው ብላቴን ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በርካታ ግጥሞችን፣ ተውኔቶች እና መጣጥፎችን ለኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ አበርክቷል፡፡

በጣም ከሚታወቁት ግጥሞቹ መካከል “እሳት ወይ አበባ፣ ዓድዋ፣ መርካቶ እና ጴጥሮስ ያችን ሰዓት” ተጠቃሽ ሲሆኑ፥ የዳኒሲዩስ ዳኝነት፣ በልግ፣ የደም አዝመራ፣ እኔም እኮ ሰው ነኝ፣ የከርሞ ሰው እና የእሾህ አክሊልን ጨምሮ ከ35 በላይ ተውኔቶችን ደርሷል፡፡

ይህ ትልቅ የጥበብ ፈርጥ የትርጉም ስራዎችንም ያዘጋጀ ሲሆን፥ ወደ አማርኛ ከመለሳቸው የትርጉም ስራዎች መካከል ሐምሌት እና ማክቤዝ ይጠቀሳሉ፡፡

የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን “Proud to be African” የተሰኘው ግጥም በፈረንጆቹ 1986 በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሕዝብ መዝሙር ሆኖ መመረጡ ይታወሳል፡፡

ሎሬት ጸጋዬ ስለ ሕዝብ፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ስልጣኔ በአጠቃላይ ያመነበትን እውነት በቅኔ ገሀድ የሚያወጣ ሲሆን፥ ስራዎቹ ከሀሳብ ጥልቅነት በተጨማሪ ስለ ለሀገሩ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩ ናቸው፡፡

ድርሰቶቹ የልብ አድርስ ከመሆናቸው በተጨማሪ በተለየና አይረሴ የግጥም አነባበብ ስልቱ ዛሬም ድረስ በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ተቀርጿል፡፡

ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ከስነ ጽሁፍ ስራ እምብዛም ሳይርቅ ለሙያው ያለውን ፍቅር ያሳየ ባለውለታ ሲሆን፥ ሩቅ ምናብ ያለውና ጥልቅ አሰላሳይ መሆኑን በርካቶች ይመሰክራሉ፡፡

ሌላው በኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ታሪክ ትልቅ አሻራ ያሳረፈው ጉምቱ ሰው ደግሞ ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሐት ገ/እግዚአብሄር ይጠቀሳል፡፡


በትግራይ ክልል ዓድዋ ርባ ገረድ የምትባል ቦታ የተወለደው ደራሲ፣ አርታኢና ጋዜጠኛ ስብሐት ገ/እግዚአብሄር በኢትዮጵያ ስነጽሁፍ በተፈጥሮአዊ የአጻጻፍ ስልቱ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡

ጋሽ ስብሐት ያለውንና የሚታየውን እውነታ ሳይበርዝ (ያለማጋነን ወይም መሸፋፈን) በሚጽፋቸው ድርሰቶቹ የፈረንሳዊውን ኤሚል ዞላ የአጻጻፍ ዘይቤ የተጋራ መሆኑን ይነገራል፡፡

በአጻጻፍ ስልቱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ገደቦችን በመሻገር የሰውን ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪና ማህበራዊ እውነታን በድፍረት በመጻፍ የሚታወቀው ጋሽ ስብሐት፥ በጽሁፎቹ ቀላል የሚመስሉ ቃላትን ቢጠቀምም በጣም የተራቀቁና ፍልስፍናን ያዘሉ ናቸው፡፡

ከስብሐት ገ/እግዚአብሄር የስነ ጽሁፍ ስራዎች መካከል “ትኩሳት፣ ሌቱም አይነጋልኝ፣ የፍቅር ሻማዎች፣ ስምንተኛው ጋጋታ፣ እነሆ ጀግና፣ እነሆ መንገድ” የተሰኙት ይጠቀሳሉ፡፡

ስብሐት ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲቋቋም በአርታኢነት ያገለገለ ሲሆን፥ የካርል ማርክስ ሥራ የሆነውን ካፒታል (Das Capital) ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በመመለስ በትርጉም ስራ ላይም ተሳትፏል፡፡

ኪነጥበብ ለማኅበረሰብ ለውጥና ሀገራዊ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ በተፈለገው ደረጃ ተደራሽ እንዲሆን ለትውልድ ተምሳሌት የሚሆኑ ሰዎችን ማስታወስ ግድ ይላል ፡፡

ትውልድ የራሱን ጀግና ይፈጥር ዘንድ እነዚህ ጉምቱ የጥበብ ፈርጦች በትውልድ እንዲዘከሩና ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቻቸው ለትውልድ ይሻገር ዘንድ በመዲናዋ ሀውልት ተቀርጾላቸዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version