አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መንግሥት ባደረገው ሪፎርም በይዘት፣ በተለወጠ አደረጃጀት እና በቴክኖሎጂ አማራጮች ተደራሽ በመሆን ተወዳዳሪነቱን አስፍቷል አሉ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት “የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
አቶ አድማሱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ተቋሙ ሰፊውን ሪፎርም በመቀላቀል ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሙያዊ ነጻነቱ የተከበረ ማድረግ ችሏል።
በይዘት፣ በተለወጠ አደረጃጀት እና በቴክኖሎጂ አማራጮች ተደራሽ በመሆን ተወዳዳሪነቱን አስፍቷልም ነው ያሉት።
ተቋሙ ከሪፎርሙ በመቋደስ ከራሱ አልፎ ሰፊ የብሮድካስት ልምዱን በማካፈል ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም ፈጠራን፣ የሐሳብ ብዝኃነትና ዓለም አቀፋዊነትን በማስፋት ተመራጭና ወቅታዊ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገለ እንደሆነ መግለጻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።

