አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን የግብርና እና የእንስሳት ሀብት ልማት በማሳደግ በሕብረተሰቡ ህይወት ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ እያደረገ ይገኛል።
የዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማጠናከር የተጀመረው ይህ መርሐ ግብር፥ በዋናነት የእንስሳት ተዋጽኦ ምርትን በማሳደግ የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥና የስራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡
ይህንን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት ከመንግሥት በኩል የተዘረጋው ጠንካራ መዋቅራዊ ድጋፍና የፖሊሲ አቅጣጫ እንዲሁም አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ያሳዩት ተነሳሽነት ለመርሐ ግብሩ ስኬታማነት ዋነኛ ምሰሶ መሆን ችሏል።
በዚህም ከ2012 እስከ 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በመንግስት እና በህዝብ የተቀናጀ ጥረት በተለያዩ የእንስሳት ምርቶች ከፍተኛ የሚባል እድገት ተመዝግቧል።
ለአብነትም ለስጋ ምርት ማቀነባበሪያዎችና አርቢዎች በተሰጠው ትኩረት በ2012 ዓ.ም 300 ሺህ ቶን የነበረውን የስጋ ምርት በ2017 ዓ.ም ወደ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን ማሳደግ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ የማር ምርትን በ2012 ከነበረው 59 ሺህ ቶን በ2017 ወደ 327 ሺህ ቶን በማሳደግ እመርታ ተመዝግቧል፡፡
በቀደሙት ዓመታት ከነበረው 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ሊትር የወተት ዓመታዊ ምርት በ2017 ዓ.ም ወደ 13 ነጥብ 7 ቢሊየን ሊትር ማድረስ ተችሏል።
በሌላ በኩል ለህጻናትና ለእናቶች ጤና እጅግ ወሳኝ የሆነው የእንቁላል ምርት በ2012 ዓ.ም ከነበረበት 2 ነጥብ 8 ቢሊየን በ2017 ዓ.ም ወደ 9 ነጥብ 4 ቢሊየን አድጓል።
እነዚህ ቁጥሮች ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የያዘችው ቁርጠኝነት ከወረቀት ባለፈ ወደ እያንዳንዱ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ቤት መግባቱን የሚያመላክቱ ናቸው።
ይህም መንግሥት ለዘርፉ መነቃቃትና እድገት ባደረገው ከፍተኛ የግብዓት አቅርቦትና ድጋፍ እንዲሁም በላባቸውና በጥረታቸው አዳዲስ የልማት ምዕራፎችን በሚጽፉ አርሶ እና አርብቶ አደሮች የጋራ ጥረት የተገኘ ውጤት ነው፡፡
እስከ 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለመላው አርሶ አደርና አምራች ማህበረሰብ 136 ሚሊየን የአንድ ቀን ጫጩቶች፣ 9 ነጥብ 2 ሚሊየን የዓሣ ጫጩቶች፣ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች እንዲሰራጩ ማድረግ ተችሏል።
የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከፍተኛ የልማት መነሳሳት የፈጠረ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ከ12 ነጥብ 5 በላይ ሚሊየን አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡
በሌማት ትሩፋት የተመዘገበው ስኬት ኢትዮጵያ ራሷን ችላ የድህነት ታሪኳን ከመቀየር ባሻገር ሌሎችን መርዳት የሚያስችል አቅም ለመገንባት አስደናቂ ጉዞ እያደረገች መሆኑን ያመላከተ ሆኗል።
የመንግሥት የልማት ራዕይና የኢትዮጵያ ህዝብ የስራ ወዳድነት ተቀናጅተው ያመጡት ይህ ታላቅ ሀገራዊ ድል ወደፊትም ለሚከናወኑ መሰል የልማት ስራዎች እንደ ትልቅ ተሞክሮና ማሳያ የሚሆን ነው።
በዮናስ ጌትነት

