አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና በሆርሙዝ ሰርጥ ጥቃት በተፈጸመበት መርከቧ ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም አለች፡፡
አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ በቻይና መርከብ ላይ ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው መሆኑ ተገልጿል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊን ጂያን እንዳሉት፥ ባሳለፍነው ሰኞ በተፈጸመው ጥቃት በመርከቡ ሰራተኞች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፡፡
ዓለም አቀፍ የነዳጅ መርከቦች በሚንቀሳቀሱበት የሆርሙዝ ሰርጥ በርካታ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችና እገታዎች አሳሳቢ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰርጡ ክፍት እንዲሆንና የመርከቦች እንቅስቃሴ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከወን የሁሉም ዓለም ሀገራት ፍላጎት መሆኑንም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡
በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በመርከቦችና ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ማስቀረት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል ከሚያልፈው የክሩድ ነዳጅ ምርት ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ለኤዢያ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን፥ ቻይና፣ ህንድ እና ጃፓን ደግሞ መዳረሻዎቹ መሆናቸውን አስታውሶ የዘገበው አናዶሉ ነው፡፡
በአቤል ነዋይ

