አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ የዓለም ዓይንና ጆሮ በባህር ሞገዶች እና በመርከቦች ድምፅ ላይ ሆኗል።
የመጫወቻ ካርዱን የሚዘውሩት ኃያላንም በጥቅም ግጭቶች እየተላተሙ ይገኛሉ። የዓለም ኢኮኖሚ ደም ሥር የሆነው ነዳጅ ዛሬም እንደ ትናንቱ ወሳኝ ነው፡፡ ሆርሙዝ ደግሞ ይህ የዓለም ኢኮኖሚ የቆመበት ቀጭን ገመድ ሆኗል።
“ባህርን የተቆጣጠረ ዓለምን ይቆጣጠራል” የሚለው ጥንታዊ ብሂል ዛሬም ዘመን ተሻግሮ ኃያላኑን ከየብስ ነቅሎ ወደ ጥልቁ ባህር አውርዷቸዋል። ከቀይ ባህር እስከ ደቡብ ቻይና፣ ከአርክቲክ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ያለው እሽቅድምድም የንግድ መስመርን የመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን፥ የዓለምን ቀጣይ የኃይል ሚዛን በመዳፍ ለመጨበጥ የሚደረግ ፍልሚያ ስለመሆኑ ሐቆች ይመሰክራሉ።
በዚህ የጂኦ-ፖለቲካ ሰሌዳ ላይ ትልቁ ፉክክር የሚካሄደው በጠባቧ የሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ነው። ይህች ሰርጥ ለኢራን ተራ ውሃ ሳትሆን፥ ስትራቴጂካዊ የቁማር ካርድ ናት። በሰርጡ ግራና ቀኝ የተሰለፉት ተፋላሚዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴም የዓለምን የነዳጅ ዋጋና የጸጥታ ሁኔታ ያዛባዋል።
የባህሩ ሰሌዳ ልክ እንደ ቼዝ ጨዋታ ነጭና ጥቁር ሆኖ አሜሪካና ኢራንን ፊት ለፊት አፋጧቸዋል።
ዝነኛው የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኝ ሮበርት ዲ. ካፕላን “Monsoon” በተሰኘው መጽሐፋቸው፥ ይህችን ሰርጥ የዓለም ኢኮኖሚ “ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓት” ይሏታል። ሆርሙዝን እንደ “መቆለፊያ” መጠቀም ሊያመጣ የሚችለውን መዘዝ ሲያብራሩም “ሆርሙዝ ከተዘጋ የዓለም ኢኮኖሚ ትንፋሽ ይቆማል” የሚል ጠንካራ መከራከሪያ ያቀርባሉ።
ይህ ፍልሚያ የቀጣዩን ክፍለ ዘመን የባህር ላይ የበላይነት ለመወሰን የሚደረግ ግብግብ ነው። ዛሬ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ መልህቃቸውን የሚጥሉበት ስፍራ ለማግኘት የሚዳክሩት ለዚሁ ነው። አሁን ላይ ባህርን መቆጣጠር የአንድ ሀገር የህልውና አምድ ሆኗል። ይህ ውጥረት ቻይና እና ሕንድን አስጨንቆ፣ የታዳጊ ሀገራትን መቀነት ፈትሿል። የባህር በር ለሌላቸው ሀገራትማ ያቺ ጠባብ ሰርጥ አማራጭ የታጣባት ብቸኛ መተንፈሻ ሆና ኢኮኖሚያቸውን አንገዳግዳለች።
ለዚህ ነው የቀይ ባህር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ፣ የኢኮኖሚ ነፃነትና የብሔራዊ ደህንነት መቆለፊያ ነው የሚባለው። የብልጽግና በርና የጂኦ-ፖለቲካው ማጠንጠኛ መሆኑን ዓለም አንገቱን በአዎንታ የነቀነቀው፣ የባህር መተንፈሻ ማግኘት ያፈጠጠ የፖለቲካ ሐቅ በመሆኑ ነው። ባህር በር የኢኮኖሚ መስመር ብቻ ሳይሆን የታሪካዊ ማንነታችን መገለጫ ነው። ኢትዮጵያ አሁን የባህር በር ባለቤት ለመሆን የምታደርገው ጥረት፣ ቀጣናው ካለው እጅግ ከፍተኛ ስልታዊ ጠቀሜታ የሚመነጭ ነው። ቀይ ባህር በዓለም ላይ ካሉ የንግድ መስመሮች እጅግ አቋራጩና በራሪው መስመር ነው።
የራስ የባህር በር መኖር ግዙፍ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ ለወጪና ገቢ ንግድ አስተማማኝ ዋስትና ይሰጣል።
ከንግድ በዘለለ፣ በቀይ ባህር ወለል ሥር የተዘረጉት የፋይበር ኦፕቲክ ኬብሎች የዓለምን የኢንተርኔትና የዳታ ትራፊክ ይሸከማሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ በዚህ ቀጣና የዳርቻ ባለቤት መሆኗ ለዲጂታል ኢኮኖሚዋና ለደህንነቷ የሚኖረው አስተዋጽኦ የላቀ ነው። ኢትዮጵያ ለዘመናት የቀይ ባህር ባለቤት ሆና የቆየች ሀገር እንደመሆኗ፣ አሁን የምታደርገው ጥረትም ተፈጥሯዊ መብቷን በሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለማስመለስ ነው።
ዛሬ የባህር ላይ ፍልሚያ ከመርከቦች ጥበቃ አልፎ የሰርጓጅ መርከቦችና የቴክኖሎጂ የበላይነት ሽኩቻ ሆኗል።
የሆርሙዝን ፍጥጫ በቼዝ ጨዋታ መስታወትነት ስንመለከተው እያንዳንዱ እርምጃ በጥንቃቄ የሚሰላበት ስልታዊ ፍልሚያ መሆኑን እንረዳለን።
በዚህ ብልህ እንቅስቃሴ ውስጥ ኢትዮጵያም በቅርቡ በራሷ ወደብ ላይ መልህቋን ትጥላለች፤ የኢኮኖሚ ነፃነቷንም ታረጋግጣለች።
በኃይለኢየሱስ መኮንን

