Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አበበች ጎበና የእልፎች እናት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ በመባል የሚታወቁት ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና ከሀገር ባለውለታነት አልፈው ለሰው ልጆች ትልቅ ክብርን በመስጠት በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች እናትም አባትም ሆነው ሰው ከወደቀበት ቀና እንዲል አድርገዋል።

ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ከጎዳና እያነሱ አጥበው፣ አብልተው፣ አስተምረው በርካታ ልጆችን ለቁም ነገር ማብቃት የቻሉ ጀግና ሴት ነበሩ።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ ውስጥ ሸበል አቦ በተባለ የገጠር መንደር በ1928 ዓ.ም የተወለዱት ክብርት ዶ/ር አበበች ጐበና፤ በወቅቱ በነበረው ባህልና ልማድ በ11 ዓመታቸው ትዳር እንዲይዙ የቀረበላቸውን ጥያቄ በብቸኝነት በመቃወም ወደ አዲስ አበባ ገቡ፡፡

በአዲስ አበባ ስራ ሳይንቁ በግለሰቦች ቤት ከማገልገል ጀምሮ በተቋም ውስጥ ተቀጥረው እስከ ምርት ክፍል ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡

ክብርት ዶ/ር አበበች (በልጆቻቸው አጠራር እዳዬ) በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ አብያተ ክርስትያናትን በማገልገል ከፍተኛ አበርክቶ ነበራቸው፡፡

በዚህም አጋጣሚ በ1972 ዓ.ም ለመንፈሳዊ ጉዞ በሄዱበት በሀገራችን ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮ ድርቅ ሳቢያ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሁለት ህፃናትን በመያዝ አበበች ጐበና ህፃናት ክብካቤና ልማት ማህበርን መሰረቱ፡፡

ክብርት ዶ/ር አበበች (እዳዬ) ለ41 ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁምነገር ያበቁ ሲሆን፤ ከዚህ ባሻገር ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡

በመሆኑም በተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ታላላቅ ሽልማቶችና እውቅናዎችን እንዲሁም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በሰብዓዊነት ዘርፍ አግኝተዋል፡፡

ክብርት ዶ/ር አበበች (እዳዬ) ድህነትን በተለይም የህፃናት ጉስቁልናን መቅረፍ የሚቻለው በግለሰብ ደረጃ ለምፅዋት በሚወረወሩ ሽርፍራፊ ሳንቲሞች ሳይሆን በአንድነት በማበር እንደሆነ ያምናሉ።

በመሆኑም ያለውን አቅም በማሰባሰብ በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን በተለይም ሴቶችን መደገፍና ማብቃት ይገባል የሚል ጽኑ እምነት ነበራቸው፡፡

እኚህ ለእልፎች እናትም አባትም ሆነው ለነገ ተስፋቸው መንገድ የጠረጉ እናት በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም በኮሮና በሽታ ምክንያት በተወለዱ በ85 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ቢያልፉም አበበች ጐበና ህፃናት ክብካቤና ልማት ማህበር ዛሬም ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት እየቀየረ ይገኛል።

አበበች ጎበና ለብዙ ኢትዮጵያውያን የቸርነት፣ የጥንካሬ እና የፍቅር ተምሳሌት ሆነው በበጎ አድራጎት ስራቸው ትውልድ ሲዘክራቸው ይኖራሉ።

Exit mobile version