Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሀገር ፍቅርን ከእናታቸው የተማሩት ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይናን ለ13 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩት ሺ ጂንፒንግ አሁን ለደረሱበት ተፅዕኖ ፈጣሪነት እና የመሪነት ደረጃ እናታቸው ቺ ዢን መሰረት እንደሆኑላቸው ይነገራል፡፡

በዓለም ላይ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና መሪዎች አሁን ላይ ለደረሱበት ደረጃ የተለያዩ የህይዎት ተሞክሮዎች እና ምሳሌ የሆኗቸው ሰዎችን በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡

የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግም አሁን ለደረሱበት ደረጃ እና የፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እናታቸው ቺ ዢን ምሳሌ ሆነዋቸዋል፡፡

ቺ ዢን በ1939 ኮሙኒስት ፓርቲን በመቀላቀል በፓርቲው ውስጥ በበርካታ የኃላፊነት ቦታ ላይ አገልግለዋል፡፡

በ1953 የተወለዱት ፕሬዚዳንት ሺ የእናታቸውን ሀገር ወዳድነት ስሜት እየተመለከቱ ስለ ሀገር ፍቅር ምንነት ተምረዋል።

ከእለታት አንድ ቀንም እናት ቺ ዢን በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰራው ጀብዱ እና ታማኝነት በቻይናውያን ዘንድ የሚዘከረውን ዩ ፌይ ታሪክ የሚያወሳ መጽሀፍ ገዝተው ለልጃቸው ሺ ሰጡ፡፡

ከዚህ የዩ ፌይ ታሪክ ለሀገር እስከ መስዋዕት የደረሰ ዋጋ መክፈልን የተማሩት ፕሬዚዳንት ሺ የህይዎታቸውን መርህ ከመጽሀፉ ቀድተዋል

በተጨማሪም ቀለል ያለ የአኗኗር ዘይቤን መከተል ሺ ጂንፒንግ ከእናታቸው ተምረዋል፡፡

ለአብነትም በ1980ዎቹ ፕሬዚዳንት ሺ በቻይና ሁቤይ ግዛት እየሰሩ በነበረበት ወቅት እናታቸው ከአስር ዓመታት በፊት ከአሮጌ ጨርቃጨርቅ የሰሩላቸውን ብርድ ልብስ ሲለብሱ ታይተዋል፡፡

ፕሬዚዳቱ አዲስ ብርድ ልብስ ቢገዛላቸውም “የእናቴ ብርድ ልብሶች ተመችተውኛል” ሲሉ መናገራቸው ለብዙዎች አግራሞትን ፈጥሮም ነበር፡፡

በፈረንጆቹ 2012 ላይ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሺ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ  ደግሞ የቻይና ፕሬዚዳንት በመሆን እስካሁን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

እንደ ታይም መጽሔት ዘገባ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ዶናልድ ትራምፕን፣ ቤኒያሚን ናታኒያሁን፣ ናሬንድራ ሞዲን እና ክላውዲያ ሼንቦም በመብለጥ ዓለማችን ካሉ ተጸዕኖ ፈጣሪ መሪዎች ቀዳሚ ናቸው፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version