አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀልጣፋና ግልፅ የታክስ አስተዳደር አገልግሎት ለኢንዱስትሪ አምራቾች ማቅረብ አስፈላጊ ነው አለ የገቢዎች ሚኒስቴር።
ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ ቢሮ በኢስተርን ኢንዱስትሪያል ፓርክ በመክፈት ስራ አስጀምሯል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ መስከረም ደበበ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በተያዘው በጀት ዓመት 13 ቢሊየን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ተችሏል።
በዚህም በርካታ አምራቾች ገብተው ስራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸው÷ ቀልጣፋና ግልፅ የታክስ አስተዳደር አገልግሎት ለኢንዱስትሪ አምራቾች ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን በመገምገም ሚኒስቴሩ ቢሮውን በኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ መክፈቱን ተናግረዋል።
የቁጥጥር ዘርፉን ለማስጨነቅ ሳይሆን የግብር ስርዓቱን ድጋፍና ክትትል እንዲሁም አገልግሎት ለማቅረብ የታሰበ መሆኑን አንስተዋል።
ግብር ከፋዩን ከመቅረብ በዘለለ ማስተማር ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ይህንን ታሳቢ በማድግ ቢሮው መከፈቱንም አስረድተዋል።
ቢሮው የህግ ግንዛቤን በመፍጠር ባለሃብቱ በአግባቡ እንዲሰራ ለማገዝ ይረዳልም ነው ያሉት።
የኢስተርን ኢንዱስትሪያል ፓርክ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሺ ያንግ በበኩላቸው÷ ቢሮው በቅርበት መከፈቱ የአምራቾችን ምርታማነት ለማሻሻል ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
በዳዊት ጎሳዬ

