Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለአፍሪካ የ23 ቢሊየን ዩሮ ኢንቨስትመንት ይፋ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአፍሪካ ሀገራት ተግባራዊ የሚሆን የ23 ቢሊዮን ዩሮ ኢንቨስትመንት ይፋ አደርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከ30 በላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በተሳተፉበት እና በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ በሚገኘው የፈረንሳይ አፍሪካ መድረክ ነው የኢንቨስትመንት ጥቅሉን ይፋ ያደረጉት፡፡

የኢንቨስትመንት ጥቅሉ በኢነርጂ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በባህርና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በግብርና ዘርፎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ይህ የኢንቨሰትመንት ጥቅል በአፍሪካ 250 ሺህ ቀጥተኛ የስራ ዕድል ይፈጥራል ነው የተባለው፡፡

ፕሬዚዳንት ማክሮን በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ እዚህ የተገኘነው በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ባለሃብቶችም በፈረንሳይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ዕድል ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ፈረንሳይ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም ከቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ እና ከአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ጋር አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

መድረኩ ከፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገራት ውጭ ሲካሄድ የአሁኑ የመጀመሪያው መሆኑን ሮይተርስ እና ፍራንስ 24 ዘግበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version