አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲፕሎማሲ የሀገር ህልውና እና ክብር መጠበቂያ መሳሪያ ነው።
ይህ የሚሆነው ግን የውጭ ግንኙነት እሳቤ እና አተያይ የጠራ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ”መደመር” በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ይህ ሐሳብ በጥልቅ ተተንትኗል።
”ሚዛናዊ ግንኙነት” የሚለው ደግሞ ተጠቃሹ ነው። ኃያላን ሽኩቻ ውስጥ በገቡበት ዓለም የአንደኛው ወገን ከመሆን ይልቅ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ባደረገ ሚዛናዊ ግንኙነት ከሁሉም ጋር በትብብር መስራት አዋጭ ነው።
ይህ ከቀደሙት ዓመታት የተለየ የኢትዮጵያ አዲስ የውጭ ግንኙነት እሳቤ እና አተያይ ዓለም ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሰራ አድርጓል።
የተለያየ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ሀገራት እና መንግሥታት ወደ ፕራግማቲኳ ኢትዮጵያ እንዲተሙም ማድረግ ችሏል።
ከሕንድ እስከ ቱርክዬ፣ ከጣሊያን እስከ እስራኤል፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እስከ ኢንዶኔዢያ፣ ከጅቡቲ እስከ ጀርመን… ሶማሊያ ብዙ ብዙ… በአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ስበት በርዕሳነ መንግሥታት የተመሙ ናቸው።
ፈረንሳይ ደግሞ በዚህ ረገድ ቀዳሚ ነች። ከ12 አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮ-ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመደመር መንግሥት ዘመን የላቀውን ምዕራፍ ተቀዳጅቷል።
ለዚህም በመሪዎች ደረጃ የተደረገውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማየት ብቻ በቂ ነው።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ይፋዊ ጉብኝታቸውን ያደረጉት በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ነበር።
ፕሬዚዳንት ማክሮን በሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝታቸው ሀገራቱ በትብብር በሚሰሯቸው የመከላከያ፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በርካታ ስምምነቶች ተፈርመዋል።
ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ እድሳት በሙያና በገንዘብ ድጋፍ የምታደርግበት ማዕቀፍ ደግሞ ሌላው ተጠቃሹ ነው።
ፕሬዚዳንቱ በላሊበላ ተገኝተው ቅርሱን መጎብኘታቸውም የሚታወስ ነው።
ማክሮን ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ደግሞ ባሳለፍነው ዓመት ታሕሣሥ ወር 2017 ዓ.ም ነበር።
በወቅቱ መሪዎቹ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ወደ ልዩ አጋርነት አድጎ ታይቷል።
በወቅቱም ፈረንሳይ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እንደምትደግፍ ፕሬዚዳንቱ ይፋ አድርገዋል።
በአንድ ቀን ቆይታቸውም በመንግሥታቸው የገንዘብ ድጋፍ የታደሰውን ብሔራዊ ቤተመንግሥት ጎብኝተዋል።
አሁን ደግሞ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአዲስ አበባ ለሦስተኛ ጊዜ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው።
ይህም በሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገ ይፋዊ ጉብኝት ሲሆን÷ የፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ አዲስ አበባ ተደጋጋሚ መምጣት ሁለት ነገሮችን ይነግረናል፡፡
እድሜ ጠገቡ የኢትዮ-ፈረንሳይ ግንኙነት በሁሉም መስክ መጠናከርና ማደጉ ቀዳሚው ሲሆን÷ ከመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤዎች ውስጥ የሚዛናዊ ግንኙነት ዘውግ ግቡን መምታቱ ደግሞ ሁለተኛውና ዋነኛው ነው፡፡

