አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ ለ2030 እና አጀንዳ 2063 ግቦች የሚያስፈልጋትን የልማት ፋይናንስ ለማግኘት የራሷን የብድር ደረጃ መመጠኛ ተቋም ለማቋቋም የሚያስችል ውሳኔ አሳልፋለች፡፡
የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት 10ኛ ዓመታዊ ኮንፈረንስ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መድረኩ በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ፣ ዘላቂ ልማት፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አስተዳደርና በተለዋዋጭ ዓለም የአፍሪካ ፈተናዎች ዙሪያ የሚያተኩር ነው።
የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትን ጨምሮ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በአሕጉሪቱ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚደረግ ጥረት ቢኖርም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሰቃዩበትና የሚሰደዱበት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ይሄውም በአፍሪካ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ÷ ከጸጥታ ባለፈ በመልካም አስተዳደር፣ በልማትና የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት አስቻይ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የልማት ፋይናንስ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው÷ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ አስተዳደር የአጀንዳ 2063 እና 2030 ግቦችን ለማሳካት እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል።
በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋሙና አሁንም ያለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ለአፍሪካ ፍላጎትና እውነታ ምላሽ የማይሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም አፍሪካን ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት ጋር ለማጣጣም የራሷን የብድር ደረጃ መመጠኛ ተቋም (Africa Rating Agency) ለማቋቋም መወሰኗን ገልጸዋል።
ይሄውም የአፍሪካ ሕብረት በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ሲሰራ ቆይቶ በፈረንጆቹ ሰኔ ወር 2026 በሞሪሼስ በይፋ እንደሚጀመር መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

