Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ማጣት ኢፍትሐዊ ነው – አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ማጣቷ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ኢፍትሐዊነት የሚያንጸባርቅ ነው አሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ።

የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት 10ኛ ዓመታዊ ኮንፍረንስ በአፍሪካ ሕብረት እየተካሄደ ነው።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በወቅቱ እንዳሉት÷ አፍሪካ ግጭቶችን በማርገብ ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን አድንቀው፤ አፍሪካ በዓለም ሁለንተናዊ እንቅስቀሴ ላይ የጎላ ሚና እንዳላት እንገነዘባለን ብለዋል።

አፍሪካ በታሪክና በዓለም ኢፍትሐዊ አሰራር የደረሰባትን በደል ለመቀልበስ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ባልወጡበት ወቅት የተቋቋሙ ዓለም አቀፍ ተቋማት አህጉሪቱ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት ማድረጋቸው ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል።

አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካ ለመፍታት የተጀመሩ ኢንሼቲቮችን መደገፍ እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አፍሪካ በወሳኝ ማዕድናትና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትልቅ አቅም እንዳላት ገልጸው፤ ሀብቷን እሴት በመጨመር ለዓለም ገበያ የምታቀርብበትን መንገድ መቀየስ ይገባል ብለዋል።

Exit mobile version