Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የማይላላው ወዳጅነት…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 129 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ መሰረት ያለው ዘመን ተሻጋሪው የሀገራቱ ግንኙነት በሁሉም መስክ እንዲጠናከር ተደርጓል።
ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ከደገፉት እና ሕጋዊ መሆኑን ከገለጹት ሀገራት መካከል አንዷ ፈረንሳይ ናት።
የታሪክ ድርሳናት እንደከተቡት የሀገራቱ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረው በፈረንጆቹ በ1897 ነበር።
በወቅቱ ሁለቱ ሀገራት የኢትዮ-ጅቡቲ የድንበር ስምምነትን በመፈራረም የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን መሰረት ጥለዋል።
የባቡር ሀዲድ ግንባታ የሀገራቱን ወዳጅነት ይበልጥ ያጠናከረው ሲሆን፤ 781 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና በፈረንጆቹ 1897 ተጀምሮ በ1917 ግንባታው የተጠናቀቀው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር በፈረንሳይ ድጋፍ የተገነባ ነበር።
ከዚያም በፈረንጆቹ 1943 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የባህል ትብብር ማዕከልን በመገንባት፣ በ1947 ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤትን በመክፈት እና በሌሎችም ሥራዎች የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በሁሉም መስክ እንዲጠናከር ሆኗል።
ይህ ግንኙነት በሀገራቱ መንግሥታት እና ሕዝቦች መካከል ሊላላ የማይችል ወዳጅነትን መስርቶ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በወቅቱ የነበረው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ጀነራል ጉሌ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል።
በፈረንጆቹ 1973 ደግሞ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅ ፖምፒዱ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። ይህም ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጎታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የጉብኝት ልውጦች እና ትብብር እየጠነከረ መጥቷል።
ለዘመናት የቀጠለው የሀገራቱ ግንኙነትም በተለያዩ ጊዜያት እና ሁኔታዎች ወደ እርስ በእርስ መጠያየቅ እና መደጋገፍ አድጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2018 ዓ.ም ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ግንኙነቱ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያድግ አስችሎታል።
በወቅቱ መሪዎቹ አሁን ያለውን ጠንካራ ትብብር ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ እና በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፈረንሳይን ከጎበኙ ከአምስት ወራት በኋላ ፕሬዚዳንት ማክሮን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተለያዩ መስኮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነቶች ተፈርመዋል።
ከስምምነቶቹ መካከል ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ እድሳት የሙያና የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግበት ማዕቀፍ አንዱ የነበረ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት ማክሮን በወቅቱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝተዋል።
ሀገራቱ የኢትዮጵያን መከላከያ ማዘመን በሚቻልበት መንገድ ላይ መስማማታቸው ሌላው የጠንካራ ግንኙነቱ ማሳያ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአራት ዓመታት በኋላ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በፈረንሳይ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ በተለይ ሀገራቱ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።
በመቀጠልም በ2017 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ ፕሬዚዳንት ማክሮን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።
ኢትዮጵያ በንግግር፣ በሰላማዊ መንገድና ዓለም አቀፍ ሕጎችን ባከበረ መልኩ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ፈረንሳይ እንደምትደግፍ እና ጥያቄው ሕጋዊ መሆኑን በወቅቱ አንስተዋል።
እንዲሁም በፈረንሳይ መንግሥት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እድሳቱ የተከናወነውን ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ሙዚየም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በመሆን ጎብኝተዋል።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶቿን በተለይም ቡናን ለፈረንሳይ ታቀርባለች፤ ፈረንሳይ በበኩሏ ለኢትዮጰያ የምታደርገው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክራ ቀጥላለች።
በአጠቃላይ የሀገራቱ ግንኙነት በፈተናዎች ውስጥ ያለፈና በየጊዜው እየታደሰ የመጣ የረጅም ዘመን ወዳጅነት ነው።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የሚያደርጓቸው ተከታታይ ውይይቶችና ስምምነቶች ግንኙነቱ ወደ ላቀ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትብብር እንዲሸጋገር መንገዶችን ክፍት እያደረጉ ቀጥለዋል።
በሶስና አለማየሁ
Exit mobile version