Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባሕር በር ኢፍትሐዊነትን የሚያወግዙት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መልክዓ ምድር የባሕር መዳረሻን መወሰን የለበትም የሚል ጽኑ አቋም አላቸው።

ኢትዮጵያ ከባሕር በር የተገለለችበት መንገድ ኢፍትሐዊ እና ታሪካዊ ስህተት መሆኑ ይታወቃል።

የባሕር በር ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ ግዙፍ ኢኮኖሚ እና ሰፊ ሕዝብ ላላቸው ሀገራት የሕልውና ጉዳይ ነው።

ሀገሪቱ ባልተገባ መንገድ የባሕር በር በማጣቷ የደረሰባትን ኢኮኖሚያዊ ጫና እና ሌሎችንም ተግዳሮቶች መነሻ በማድረግ ተገቢ፣ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ ጥያቄ አንስታለች።

ይህ የፍትሐዊነት ጥያቄ እንደ ኢትዮጵያ መልክዓ ምድር የባሕር መዳረሻን የወሰነባቸው ሀገራት ጭምር አጀንዳ ነው።

በዓለም ከ30 በላይ ሀገራት ባሕር በር ስለሌላቸው የማደግ ዕድላቸው ተገድቧል። ይህ ደግሞ ኢፍትሐዊነትን አስፋፍቷል።

በ2017 ዓ.ም ሐምሌ ወር 3ኛው የተባበሩት መንግሥታት በማደግ ላይ ያሉ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ጉባኤ በቱርክሜኒስታን በተካሄደበት ወቅት የኢፍትሐዊነቱ ጉዳይ በስፋት ተነስቷል።

በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊው የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በርከታ ተግዳሮቶች እንደሚጋረጡባቸው፣ ዕድገታቸው እንደሚወሰን፣ በከፍተኛ የወጪ ንግድ ትራንስፖርት እንደሚበዘበዙ እንዲሁም የደኅንነት ፈተናዎች እንደሚገጥሟቸው አስረድተዋል።

የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የሚደርስባቸው ተጽዕኖ ከባድ በመሆኑ ችግሩ በጋራ መቀረፍ እንዳለበት ማሳሰባቸውም የሚታወስ ነው።

ኢፍትሃዊ የዓለም ንግድ ስርዓት ከዛሬዋ የተሳሰረች ዓለም እውነታዎች ጋር ያልተጣጣመ ያለፈው የቅኝ ግዛት ዘመን ውርስ መሆኑን በመጠቆም÷ የባሕር በር ስለሌለው ወደኋላ ሊተው የሚገባ ሀገር መኖር እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የያኔው ሊግ ኦፍ ኔሽን የዛሬው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ተልዕኮውን የዓለምን ሰላም ማስጠበቅ አድርጎ ሲመሰረት÷ ቻርተሩን ከፈረሙ ቀዳሚ መሥራች ሀገራት መካከል የነበረችው ኢትዮጵያ የዓለም ሰላም እንዲረጋገጥ እና ፍትሕ እንዲሰፍን በቁርጠኝነት ሰርታለች።

80 ዓመታት ባስቆጠረው የመንግሥታቱ ጉዞ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር፣ በጸጥታ እና ደኅንነት እንዲሁም በልማት ትብብር በንቃት በመሳተፍ አሻራዋን እያሳረፈች ትገኛለች።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአፍሪካ ሕብረት-የተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ ኮንፈረንስ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ይገኛሉ።

በብርሃኑ አበራ

Exit mobile version