አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከዓለም አትሌቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጆን ረጂዮን ጋር ተወያይተዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በስፖርት ስትራቴጂካዊ ዕድሎች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የውይይቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ የ2028 አልቲሜት ሻምፒዮንሺፕ እና የ2031 የአትሌቲክስ የዓለም ሻምፒዮና ለማዘጋጀት የቀረበውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞች እና ሌሎች የስፖርት መሰረተ ልማቶችን መገምገምን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቅርቡ ከተማችን ከሶስት በላይ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶችን በብቃት ማስተናገዷን አስታውሰዋል።
ታላላቅ የስፖርት ሁነቶችን ለማስተናገድ ብሎም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚያስችል የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ስልጠናዎችን በማስፋፋት እና የህዝባችን እንግዳ ተቀባይነትን ለልዑካኑ ገለጻ አድርገናል ነው ያሉት።
የዓለም አትሌትክስ ዋና ስራ አስፈፃሚው በበኩላቸው፤ በአዲስ አባባ እየታየ ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ እና መንግሥት የስፖርት ሁነቶችን ለማካሄድ ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ተቋሙ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት ለመስራት ያለውን ፍላጐትም አስታውቀዋል።

