Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ዓመታዊ ጉባኤ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 10ኛው የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ዓመታዊ ጉባኤ 26 ነጥብ ያለው የጋራ አቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቅቋል።

ጉባዔው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በተገኙበት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ ሁለቱ መሪዎች በድርጅቶቻቸው መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ አቋም ይዘዋል።

በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ፤ በአህጉሪቱ ሰላምና ጸጥታ፣ ሰብአዊ መብት እና ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063ን እና የ2030 ዓለም አቀፍ የልማት ግቦችን ለማሳካት በትብብር መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በሰላም እና ጸጥታ ዘርፍ በአህጉሪቱ የተለያዩ ቀጣናዎች ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት መክረው፤ ግጭቶች እና ውጥረቶች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ለሚመራቸው የሰላም ማስከበር ስራዎች አስተማማኝ እና ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ እንዲኖር በጋራ ለመስራት ቃል ገብተዋል።

ከዘላቂ ልማት ጋር በተያያዘ መሪዎቹ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአፍሪካን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ እና የልማት ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ መዋቅራዊ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት በአፍሪካ ኢኮኖሚ፣ በምግብ ዋስትና እና በኃይል አቅርቦት ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ለመቅረፍ በቡድን 20 እና በቡድን 7 ስብሰባዎች ላይ የአፍሪካን ድምጽ በጋራ ለማሰማት ተስማምተዋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ የሥራ ዘመናቸውን ለሚያጠናቅቁት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለአፍሪካ ሰላምና ልማት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

Exit mobile version