Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ስታስጠራ የቆየችው አትሌት የብርጓል መለሰ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያዊቷ የረጅም ርቀት ሯጭ አትሌት የብርጓል መለሰ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ስታስጠራ ቆይታለች፡፡

አትሌት የብርጓል ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጀምሮ በበርካታ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ በመካፈል ስኬታማ ጊዜያትን በአትሌቲክሱ አሳልፋለች፡፡

አትሌቷ በተለያዩ ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል ከመሳተፍ ባለፈ ለሀገሯ ሜዳልያዎችን ማስገኘት ችላለች፡፡

በፈረንጆቹ 2015 በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ሀገሯን ወክላ በግማሽ ማራቶን ውድድር የነሐስ ሜዳልያ ማሸነፏ ይታወሳል።

እንዲሁም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ማስጠራት የቻለች አትሌቷ÷ በዚያው ዓመት በቺካጎ ማራቶን የብር ሜዳልያ ባለቤት ነበረች፡፡

በሻንጋይ፣ ፕራግ እና ሂውስተን ማራቶኖችም በቀዳሚነት ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

በፓሪስ ግማሽ ማራቶን ውድድር ሁለት ጊዜ ድል የተቀዳጀች ሲሆን÷ በሊዝበን ግማሽ ማራቶን ውድድርም በቀዳሚነት ማጠናቀቋ አይዘነጋም፡፡

በቀጣይ በካናዳ በሚካሄደው የኦታዋ ማራቶን በመሳተፍ ሀገሯን ለማስጠራት ሕልም የነበራት አትሌት የብርጓል መለሰ ከትናንት በስቲያ በድንገት ሕይወቷ ማለፉ ይታወቃል፡፡

ሚያዚያ 1982 ዓ.ም የተወለደችው አትሌቷ ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ማለዳ በጃን ሜዳ የስፖርት ማዘውተሪያ ባገጠማት ድንገተኛ አደጋ በ36 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።

የአትሌቷ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6 ሰዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን የሚፈጸም ይሆናል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version