አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኃያላኑ በአሁኑ ወቅት በምድር ጦር እና በአየር ኃይል የበላይነትን ከማረጋገጥ እንዲሁም የማይበገር ባህር ኃይል ከመመስረት ተሻግረው በሕዋ ጭምር ታላቅነታቸውን ለማስመስከር ጨረቃ ላይ እስከማረፍ ደርሰዋል።
በዚህ የዓለም የፉክክር መድረክ ውስጥ የአፍሪካ እንቅስቃሴ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ሀያላኑም ይህን አቅም የፈጠሩት እንዲሁ በቀላሉ አይደለም።
አፍሪካውያን ምንም እንኳን በተጨባጭ ተግባር ባይታይም ጠንክሮ ለመውጣት መተባበር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሲገልጹ መስማት የተለመደ ነው።
ይህ እንደሚያስቆጫቸው የሚናገሩት የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፥ አፍሪካውያን ጠንካራ እና ተፎካካሪ ለመሆን የጋራ ተጠቃሚነትን ማጉላት፣ አንድነትን ማጠናከርና ሀብታቸውን በጋራ መጠቀም ይጠበቅብናል ይላሉ።
በተለይም ከባሕር በር ኢፍትሃዊ አጠቃቀም ጋር በተገናኘ የሰላ ትችት የሚያነሱት ፕሬዚዳንቱ፥ ይህ ሁኔታ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚፈጥር መሆኑን ደጋግመው አሳስበዋል፡፡
የባሕር በር ያላቸው ሀገራት መተላለፊያውን በብቸኝነት ለመያዝና ለመቆጣጠር መፈለጋቸው የጤነኝነት ምልክት እንዳልሆነ በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡
የባህር በር አልባዋ ሀገር ዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ የባሕር በር ጉዳይን በሕንጻ እና በግቢው ይመስሉታል።
ይህን ሲያብራሩም፡- አንድ ትልቅ ሕንጻ ያረፈበት ግቢ ለሕንጻው የመጀመሪያ ወለል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሕንጻው ወለሎች የጋራ መጠቀሚያ እንደሆነ ያነሳሉ።
የባህር በር የሌላቸውን የዓለም ሀገራት በባህር ግቢ ውስጥ እንደሚኖሩ የምድር አንድ ወለል አድርገው የመሰሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ከባህር መጠቀም ያለባቸውን መጠቀም ይኖርባቸዋል የሚል ጽኑ መከራከሪያ ሃሳብ ያቀርባሉ።
ሕንጻው ያረፈበት ግቢ ባለቤትነት ከታች ላለው ብቻ ሳይሆን ከላይ ላለው ወለልም ጭምር በመሆኑ ከባህር የመጠቀም መብትም በዚህ አውድ መታየት እንዳለበት ያስረዳሉ።
የሕንጻው የመጀመሪያው ወለል ላይ የሚገኙ ማለትም የባህር ዳርቻ ላይ የሚገኙ ሀገራት በብቸኝነት ለመያዝ መፈለጋቸውን የጤንነት ምልክት አይደለም የሚሉትም ከዚሁ አንጻር ነው።
ስለሆነም አፍሪካ ውስጥ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የሚያጋጥማቸው ችግር ቀጣናዊ መልክ ከመያዙና የቀውስ ምንጭ ከመሆኑ በፊት በጋራ የመበልፀግ መርህን በመከተል ነፃ የመተላለፊያ መብት ሊያገኙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዚህም የባህር በር ያላቸው ሀገራት ለሌላቸው ይህን እድል በመፍቀዳቸው የገበያ ትስስር፣ የተረጋጋ ቀጣና፣ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖን ከፍ ማድረግ በአጠቃላይ የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያገኙ አስረድተዋል።
የባሕር በር ጉዳይን በአንድ አፍሪካዊ የወንድማማችነትና ፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ በመፍታት አፍሪካውያን በትብብር ጠንካራ ሆነው መውጣትና በዓለም የፉክክር መድረክ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡
ኡጋንዳ ከኬንያው የሞምባሳ ወደብ ላይ ጥገኛ በመሆኗ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ስትዳረግ የቆየች ሀገር ናት።
በሀገሪቱ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ከመምጣቱ በተጨማሪ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶቿ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ምክንያት ሆኗል።
ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘትን ጉዳይ የፖለቲካ አጀንዳ ሳይሆን የህልውናዋ ጉዳይ አድርጋ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እየሰራች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መልማት፣ ማደግ እና ሰላም መሆን ለቀጣናው ዕድገት በጎ ሚና እንደሚጫወት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
የቀይ ባህር ጉዳይ እንዴት የእኛ ሆነ፣ እንዴት ከእኛ ሄደ፣ እንዴት ማግኘት እንችላለን የሚሉት ጥያቄዎች ምርምር ይፈልጋሉ የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር በር አስፈላጊነት ላይ ግን ኢትዮጰያዊያን የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንዳለብን አሳስበዋል።
በብርሃኑ አበራ

