አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለሁሉም ሀገራት ሚዛናዊ ልብ አላት፡፡ ከሁሉም ጋር በመተባበርና በመከባበር፣ በፍትሃዊነትና በእኩልነት እንዲሁም በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ታራምዳለች፡፡
ይህ አቋሟ ጎረቤትን እንደራስ እንዲሁም የሩቁን ለጋራ ጥቅም ያስፈልጋሉ ብላ እንድታምን እና በእኩል ዓይን እንድታይ ያደርጋታል፡፡
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ሀገሪቷን ከተነጣይነት ወደ ሀገር በቀል መደመር፣ ከማይስማማት እና ከአንዱ ወገን ከተቀዳው ርዕዮት ይልቅ ወደ ጋራ ተጠቃሚነት አሸጋግሯታል፡፡
ይህ ሀገር በቀል የመደመር እሳቤ ርዕዮተ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህም እሳቤ የተረጋጋ ዓለም እና ሀገር እንዲገነባ ከመሻት የተነሳ ነው፡፡ የተረጋጋ ዓለም እና ሀገር ለመገንባት ደግሞ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠር አስፈላጊ ነው ብላ ታምናለች፡፡
በዚህ ጽኑ አቋሟ ሀገሪቷ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲኖራት አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም፣ የጋራ ተጠቃሚነትና ብልፅግና ይጠቅማሉ ያለቻቸውን ተቋማት ከመስራችነት እስከ አባልነት በመቀላቀል ሚናዋን ስትወጣ ቆይታለች፡፡ ይህ ታሪኳ ነው፡፡
ለዚህም ነው በፈረንጆቹ 1923 ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ማህበር በአባልነት ተቀባይነት አግኝታ ለዓለም እኩልነትና ሰላም በፍትህ አደባባይ እንድትታገል ያስቻላት፡፡
ከ1945 ጀምሮ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት አባል ሆና እስካሁን በተፅዕኖ እንድትዘልቅ አድርጓታል፡፡
ለሰላም ፅኑ እምነት ያላት ሀገራችን በተባበሩት መንግሥታት የመጀመሪያዋ ተልዕኮ ባሕር ተሻግራ 1951 ወደ ደቡብ ኮሪያ በመዝመት ሚናዋን ተወጥታለች፡፡
ኢትዮጵያ በተቋማት ግንባታ በማመኗ ሚናዋን በየዘመኑ እንድትወጣም አስችሏታል፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግሥታቱ ማህበር፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የምሥራቅ አፍረካ በይነ መንግሥታት የልማት ድርጅት፣ የብሪክስን ጥምረት እና የሌሎችም ድርጅቶች በመመስረትና በመቀላቀል በዓለም አቀፍ ሰላም፣ ልማት እና ብልጽግና ሚናቸውን እንዲወጡ ጉልህ አስተዋጽዖ ካበረከቱ ሀገራት አንዷ ናት።
ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ በመደመር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ሁሉን አቃፊ ናት፡፡ ከማንም ጋር የበለጠ የቅርብ እና የባሰ ሩቅ የሚባል የርዕዮተ ዓለም የፍልስፍና የተለጣፊነት ግንኙነት እንዲኖራት አትሻም፡፡
በመሆኑም በመርህ ላይ በተመሠረተ እኩልነት ላይ ቆማ በሀገር በቀሉ የመደመር ርዕዮተ ኢትዮጵያ የማንም ጥቅም ሳይጎዳ በወንድማማችነት እና እህትማማችነት ፍልስፍናዋ በጋራ መበልጸግን ተያይዛዋለች፡፡
ይህም የቀድሞው መልካም ጅምሮች እንዲቀጥሉ እና አዳዲስ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት እንዲከወኑ አስችሏል፡፡
ለሰላም ማስከበር እንኳን ስትሄድ ለጋራ ሰላምና ተጠቃሚነት በማሰብ ነው ዋጋ የምትከፍለው፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ስር ባሕር ተሻግራ ደቡብ ኮሪያ የዘመተችው ሰላም ወዳዷ ኢትዮጵያ÷ በአፍሪካ ሕብረት ተልእኮ ስርም እስካሁን በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ዘመቻ ትልቅ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች፡፡
በሰላም ማስከበሩ ያረጋገጠችውን የዓለም አቀፋዊ ተቋማት ተሳትፎ በዓለም የዲፕሎማሲ አደባባዮችም ቢሆን ብሔራዊ ጥቅሟን እያስጠበቀች ትገኛለች፡፡
የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኝነት የተፈረጁትን የአልሸባብ እና የአይኤስ ሽብርተኞችን ለመመከት ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው፡፡
በተጨማሪም በሶማሊያ የሀገር ውስጥ የጸጥታ ኃይሎችን በማሰልጠን እና ሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን በማመቻቸት ሚናው ትልቅ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ጎረቤቷ በየወቅቱ በሚፈጠሩ ተፅዕኖዎች እንዳትናጥ እና ለጋራ ሰላም ስትል የምትከፍለው ዋጋ ነው፡፡
በየወቅቱ በተፅዕኖ የማይረበሽና የተረጋጋ ሀገር መገንባት የሚቻለው ደግሞ በተቋማት እንደሆነ ታምናለች፡፡ ለዚህም ነው በአሕጉር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አባል በሆነችባቸው ተቋማት ሁሉ ሚናዋን እያሳደገች የመጣችው፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ባሻገር የሰላም አስከባሪ ኃይሎቿን በላይቤሪያ፣ ደቡብ ሱዳን እና በሩዋንዳ አዝምታለች፡፡ ጦሯ በሩዋንዳ ለሲቪሎች ሰብአዊ እርዳታ እና ጥበቃ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ጥረታቸው ለእነዚህ ሀገራት መረጋጋት እና ማገገም አስተዋፅኦ በማድረግ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሰላምና ብልፅግና ያላትን ቁርጠኝነት አሳይቷል።
በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረው የአሁኑ የመደመር የዲፕሎማሲ መርህ ደግሞ ይበልጥ የኢትዮጵያን የዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከፍ አድርጎታል፡፡ ይህም የቀድሞዎቹን ወረቶችና መልካም ጅምሮች በማስቀጠል አዲስ ታሪክ እንዲጻፍ አስችሏል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረትን ስትቀላቀል በርዕዮተ ዓለም ከመታጠር እና ከመነጠል በመውጣት አተያይ ይበልጡኑ በዓለም አቀፍ ተቋማት ምስረታ እና የአባልነት ተሳትፎ ያላት ታሪካዊ ሚና እያደገ መምጣቱን አሳይቷል፡፡
ይህም ሀገሪቷ በሀገር በቀሉ ርዕዮተ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ለተቋማት ግንባታ ያላትን ሚና ያሳያል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠንካራ ተቋማት ከሌሉ ጠንካራ ሀገርና የተረጋጋ ዓለም መፍጠር አስቸጋሪ እንደሆነ በማመን ኢትዮጵያ ብሪክስን ስትቀላቀል የኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ የተቋማት ተሳትፎ እና ሚና ከፍ ያደረጉበት ውሳኔ ስለመሆኑ ልብ ይሏል፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያ ብሪክስ ለጋራ ሰላም፣ ደኅንነት፣ ኢኮኖሚ እና ልማት መጠናከር ግንባር ቀደም ሚና እንደሚኖረው ታምናለች፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ ጥምረቱ በርዕዮተ ዓለም ላይ ሳይታጠር ሁሉንም ሀገራት በፍትሃዊነት እንዲያገለግል ትፈልጋለች፡፡
በዚህ ውስጥም በተደመረ አቅም ዓለም አቀፍ ስርዓትን ለመገንባት ሚናዬን እየተወጣሁ ብሔራዊ ጥቅሜን አስከብራለሁ ብላ ታምናለች፡፡
ኢትዮጵያ በየወቅቱ የሚፈጠሩ ተፅዕኖዎች ሀገራትን እና ዓለምን እንዳይንጡ ፍላጎቷ ነው፡፡ ይህንንም በዲፕሎማሲ ሚናዋ አሳክታለች፡፡ በዚህም ብሔራዊ ጥቅሟን እና ክብሯንም እያስከበረች መጥታለች፡፡
በዲፕሎማሲው መድረክ እና በተግባር ደግሞ በሀገር ደረጃ ወረትን በመለየት ለጋራ ተጠቃሚነት የተሰራው የልማት ስራ ለዚሁ የስበት ማዕከል ነው፡፡
በአዲስ አበባ የተሰራው የልማት ስራ ኢትዮጵያን የዓለም መድረክ የስበት ማዕከል አድርጓታል፡፡
በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የተቀዳጁና ግዙፉ ምጣኔ ሃብታዊ አቅም የገነቡ ሀገራት በብዝኃ ዘርፍ ግንባር ቀደም የሆኑት ሀገራቸውን በሚመጥን መልኩ ተቋማትን በመገንባት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያን የሚመጥን አስተማማኝ የኃይል ሚዛን ለመፍጠር በርዕዮተ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ በፅናት ተቋማትን መገንባት አስፈላጊ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
ይህም ለሁሉም ችግር ከውጪ እሳቤ በመቅዳት መፍትሔ ከመፈለግ አውጥቶ ተቋማት በሀገራዊ የመደመር እሳቤ ዘመንን ተሻጋሪ እንዲሆኑ፣ በግለሰቦች ይሁንታ የማይለዋወጡ፣ ነጻ እና ገለልተኛ፣ በእውቀትና በመርህ የሚመሩ እንዲሆኑ እና ያለአድልዎ ለጋራ ሀገራዊ ጥቅም እንዲቆሙ ያደርጋል፡፡

