አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ባለፉት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 8 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል አሉ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በግብርና ምርቶች የኤክስፖርት ቢዝነስ እንዲሁም በቡና ቅምሻና ደረጃ አወጣጥ ዘርፍ ለሦስት ወራት ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ባለፉት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 8 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ገልጸው÷ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ገቢውን ወደ 10 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አካዳሚ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ አበረታች ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው÷ ዘመናዊና ውጤታማ የወጪ ንግድ ሥርዓት ለመገንባት በዕውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል ማፍራት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የዛሬዎቹ ሰልጣኞችም የወጪ ንግዱን በዕውቀትና በክህሎት ለመምራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መርጊያ ባይሳ በበኩላቸው÷ የወጪ ንግድ በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት፣ በዕውቀትና በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የወጪ ንግድ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የደረጃ አወጣጥና የጥራት ቁጥጥር ስልጠናዎች በምርት ገበያ አካዳሚ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
አካዳሚው ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በቡና ቅምሻ ዘርፍ ብቻ ከ3 ሺህ 200 በላይ ሰልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን÷ በዘንድሮው ዓመት በግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ ቢዝነስና በቡና ደረጃ አወጣጥ 168 ባለሙያዎች ማስመረቁን አስታውቀዋል።
እንዲሁም ከ8 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የአካዳሚውን ተሞክሮና ልምድ እንደቀሰሙ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

