አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ኢትዮጵያ በብዝኃ ቋንቋና ማንነት የደመቀች ሀገር ናት አሉ።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት “የባህል ልማት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ የባህልና ቋንቋ ሳምንት በዛሬው ዕለት ተከፍቷል።
መርሐ ግብሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም ከሁሉም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አሰተዳደሮች የተወጣጡ ልዑካን በተገኙበት ነው በይፋ የተከፈተው።
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ በብዝኃ ቋንቋና ማንነት የደመቀች ሀገር መሆኗን ገልጸው÷ ፕሮግራሙ እኛነትን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ ነው ብለዋል።
የባህልና ቋንቋ ሳምንቱ ከዛሬ ጅመሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን÷ የብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋ፣ ኪነ-ጥበብ፣ እደ ጥበብ፣ የሥነ ውበት ውጤቶች፣ ባህላዊ እሴቶች ይቀርቡበታል።
በሜሮን ፈለቀ

