በምርጫ ሂደት ውስጥ ከቅድመ ምርጫ ዝግጅት ጀምሮ ውጤቱ እስኪታወቅና ይፋ ሆኖ ለአሸናፊዎቹ የአሸናፊነት ማረጋገጫ እስከሚሰጥበት እንዲሁም ቅሬታ ካለ ቅሬታ የመስማት ሂደቱ የሚከናወንበት የድህረ ምርጫ ክንውን ድረስ ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ የምርጫ ዑደት(Electoral cycle) ይባላል፡፡
የምርጫ ዑደት ሦስት ዋና ዋና ክፍሎችን ያቀፈ ነው፡፡ እነርሱም ቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ጊዜ እና ድህረ ምርጫ ናቸው፡፡
ሀ. ቅድመ ምርጫ:-
ቅድመ ምርጫ፣ ከድምፅ መስጫ ቀን በፊት ያለው ነው፡፡ አብዛኛው የምርጫ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ወቅት ነው፡፡
በቅድመ ምርጫ ወቅት፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅት እና ምዝገባ፣ የህግ ማእቀፍ ዝግጅት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ፣ ሥልጠና እና ምደባ፣ የምርጫ ክልልን የማካለል ሥራዎች፣ የመራጮች ምዝገባ፣ የፆታ አሳታፊነት፣ የብዙሃን ማኅበራት አሳታፊነት፣ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት፣ የምርጫ ጣቢያ አደረጃጀት፣ የዕጩዎች ምዝገባ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ፣ የብዙሃን መገናኛዎች የሥራ እንቅስቃሴዎች በስፋት እና በጥልቀት የሚሠሩበት ወቅት ነው፡፡
ይህ ወቅት በምርጫ አስፈጻሚው ተቋም እንዲሁም በሌሎች ባለድርሻ አካላት መጠነ ሰፊ ዝግጅት የሚደረግበት ጊዜ ነው፡፡
ለ. የምርጫ ወቅት:-
በምርጫ ዑደት መሠረት በምርጫ ወቅት በርካታ ወሳኝ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡
የድምፅ አሰጣጥ፣ ቆጠራ፣ ውጤት አገላለጽ እና ማረጋገጥ፣ እንዲሁም፣ የቅሬታ አቀራረብ እና አፈታት በዚህ ምዕራፍ የሚካተቱ ተግባራት ናቸው፡፡
ሐ. ድኅረ ምርጫ:-
በድህረ ምርጫ፣ የተሰጠው ድምጽ ቆጠራ ተከናውኖ የምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ ያለው ጊዜ ነው፡፡
በዚህ ወቅት፣ የድህረ ምርጫ ግምገማ፣ በህጋዊ ማእቀፎች መሠረት የምርጫ ክልል ማካለል እና የተቋሙን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ዝግጅት እና የመሳሰሉትን ሰፊ ሥራዎችን ያካትታል፡፡
ኢትዮጵያ ትመርጣለች!

