አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሁኑ ወቅት የአምራች (ማኑፋክቸሪንግ) ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሀገራችንን የኢኮኖሚ መዋቅር በመቀየር የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻልና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ረገድ የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
የመደመር መንግሥት ይህ ዘርፍ ያለውን ግዙፍ አቅም በመገንዘብ ምርታማነትን በማሳደግ የሀገራዊ ብልጽግና ዋነኛ ማሳኪያ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ይዟል።
በመደመር ዕሳቤ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው ይታመናል።
በዚህም መሠረት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ፖሊሲና ስትራቴጂ አዲስ በሆነ መልክ በመቅረፅ፣ ዘርፉን ለተሟላ መዋቅራዊ ሽግግር ዝግጁ ማድረግ ተችሏል።
በተለይም “ኢትዮጵያ ታምርት” ብሔራዊ ንቅናቄን በማካሄድ በዘርፉ ለዓመታት የነበሩ ማነቆዎችን ለመፍታት በተደረገው ጥረት ለዘላቂ ልማት የሚሆን ጠንካራ መሠረት ተጥሏል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ መንግሥት ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከወሰዳቸው ርምጃዎች ውስጥ በሀገር ውስጥ መመረት እየቻሉ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በስፋት እንዲመረቱ ማድረግ ነው።
የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጨምርና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንዲፈጠር የተደረገው ጥረት የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚዎች ተሳትፎ እንዲጨምር አድርጓል።
መንግሥት ለዘርፉ የሚያደርገውን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በማሻሻል፣ ዘመናዊ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ነጻ የኢኮኖሚ ዞኖች ተቋቁመው ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል።
በቅርቡ ደግሞ በነፃ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ከታክስ ነፃ መብቶች በተጨማሪ ከገቢ ግብር ነፃ እንዲሆኑ መወሰኑ መንግሥት ለዘርፉ ያለውን ልዩ ትኩረት ያሳያል።
እነዚህ ስትራቴጂያዊ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ የጀመሩ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 65 በመቶ በማሳደግ ከፍተኛ ዕድገት ተመዝግቧል።
ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት በተደረገው ልዩ ጥረት በ2015 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም በ2017 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የአምራች ዘርፍ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል።
ይህ ስኬት በዜጎች ሕይወት ላይ በተለይም በሥራ ፈጠራ፣ በምግብና በአገልግሎት ተደራሽነት ላይ አዳዲስ ዕድሎችን ፈጥሯል።
የኢኮኖሚ መዋቅሩም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረለት ይገኛል።
መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ዘርፉን ይበልጥ ለማጠናከርና የጀመራቸውን አበረታች ሥራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ግልጽ ዕቅዶችን ይዟል።
የኢንዱስትሪ ዕቃዎችና ምርቶች በጥራትና በፍጥነት ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ እንዲደርሱ ከመሥራት ባለፈ፣ ተሽከርካሪዎችን፣ ኬሚካሎችን፣ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ማሽኖችን፣ የሕክምና መሣሪያዎችንና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በስፋት ለማምረት ታቅዷል።
የዘርፉን የሰው ኃይል ዕውቀትና ክህሎት ለማልማት የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት የሥልጠናና የኢንኩቤሽን ማዕከላት ግንባታም ትኩረት ይሰጠዋል።
በተጨማሪም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሕግና የአሠራር ማዕቀፎችን በማዘመን፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የሀገራዊ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ የአምራች ኢንዱስትሪው የዕድገት ማዕከል ሆኖ እንዲቀጥል ይደረጋል።

