Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አሁናዊ ሂደትን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያየ፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ መድረኩ ፓርቲዎች በምርጫ ዝግጅት ላይ ባጋጠሟቸው ችግሮች ላይ ተወያይቶ መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡

ቦርዱ ለድምፅ መስጫ ቀን በቀሩት ጥቂት ጊዜያት ከማን ምን ይጠበቃል በሚለው ጉዳይ ላይ ከፓርቲዎቹ ጋር መምከሩን ተናግረዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአካል ተገናኝቶ ከመወያየት በተጨማሪ የመረጃ ልውውጡን ለማቀላጠፍ ዲጂታል አማራጮችን እንደሚጠቀም ነው የገለጹት።

በውይይቱ የተሳተፉ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ የተደለደለው ገንዘብ ውስንነት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታና በዕጩዎች ላይ የሚደርስ ማዋከብን ጨምሮ አጋጥመዋል ያሏቸውን ችግሮች አንስተዋል፡፡

በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ላይ ባሉ አስፈጻሚዎች የደንብ መተላለፍ እየተፈጸመ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ፥ የድምፅ መስጫ ቀን እንዲራዘም ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ሰብሳቢዋ በሰጡት ምላሽ ፓርቲዎች ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ቅሬታዎቻቸውን በማስረጃ አስደግፈው እንዲያቀርቡ አስገንዝበዋል፡፡

Exit mobile version