Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!!

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የመንግሥት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የታየበት ሀገርን በጸና መሠረት ላይ የማቆም ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተለያዩ ክልሎች የተወካዮችን ምልመላ በስኬት በማጠናቀቅ እና ለሀገራዊ ውይይት የሚሆኑ አጀንዳዎችን በስፋት በማሰባሰብ፣ ለአካታችና ዘላቂ መግባባት የሚሆን ጠንካራ የቅድመ-ምክክር ሥራዎችን አከናውኗል ።
ኮሚሽኑ በሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም የአስተዳደር እርከኖች የሚገኙ የማህበረሰብ ተወካዮችን ለመለየት ባደረገው ጥረት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና ልዩ ልዩ የሙያ ማኅበራት በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ ሂደቱ አካታችና ህዝባዊ መሠረት ያለው እንዲሆን ተደርጓል።
ይህ ተግባር መንግሥት ለምክክር ሂደቱ ስኬታማነት የሰጠውን ትኩረትና የዜጎችን የባለቤትነት ስሜት በተግባር ያረጋገጠ ሲሆን ለዘላቂ ሀገራዊ መግባባት መፈጠርም ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትም ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን ለዘመናት ሲያከራክሩ የነበሩ አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ አስችሏል።
ይህ ሂደት መንግሥት በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውስጥ የመድብለ-ፓርቲ ሥርዓትና የሰላማዊ ውይይት መንገድ እንዲቀድም ያለውን ፅኑ አቋም በተግባር ያሳየበት ነው።
በምክክር ሂደቱ ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሂደቱ እንዲሳተፉ እና የራሳቸውን አጀንዳ እንዲያቀርቡ የተደረገው ጥረት የምክክሩን አካታችነት ከሚያሳዩ ስኬቶች መካከል ቀዳሚው ነው።
ኮሚሽኑ የፖለቲካ ኃይሎች በጋራ የሚመክሩበትን መድረክ በማመቻቸት፣ ከዚህ ቀደም በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ አካላት በአንድ አዳራሽ ውስጥ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ አድርጓል።
ይህ ውጤት በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ “የመደማመጥ ባህልን” በማዳበር ረገድ እንደ ትልቅ ምዕራፍ የሚወሰድ ሲሆን ልዩነቶችን በሃሳብ የበላይነት ለመፍታት የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ጅምር ሆኖ ተመዝግቧል።
በምክክሩ የእከስካሁን ጉዞ የተከናወኑ ተጨባጭ ሥራዎችና የተገኙ ስኬቶች ኢትዮጵያ የቆየ መዋቅራዊ ችግሮቿን በዘላቂነት ለመፍታትና ጠንካራ የሀገረ-መንግሥት ግንባታን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
Exit mobile version