አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለ41ኛ ዙር በህክምና ትምህርት ያሰለጠናቸውን 444 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከህክምና ዶክተሮች በተጨማሪ በሰብ ስፔሻሊቲ፣ በሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ የህክምና ተማሪዎችን አስመርቋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ልጅዓለም ጋሻው÷ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 70 ዓመታት በህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በርካታ የህክምና ባለሙያዎችን በማስመረቅ ብቃት ያለው የሰው ሀይል እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዓመት ከ13 ሚሊየን በላይ ተመላላሽና ተኝቶ ታካሚዎችን የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል እያስተናገደ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመጪው ዓመት ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው÷ ተመራቂ ተማሪዎች ለጤናው ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የማይተላለፍ በሽታ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በመጠቅስ፤ በህክምና ዕጦት ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎችን በመታደግ ረገድ ተመራቂ ተማሪዎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በምናለ አየነው

