አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ በምራብ ሸዋ ዞን ከ362 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውን የሾቦካ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መርቀው አገልግሎት አስጀመሩ፡፡
ፕሮጀክቱ ህብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲያጋጥመው የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የተገነባ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ፕሮጀክቱ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው ሲሆን፤ ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት በማግኘታቸው ደስተኞች መሆናቸው ተመላክቷል።
በተለይም ከዚህ በፊት ረጅም ርቀት ተጉዘው ውሃ በመቅዳት ለእንግልት ሲዳረጉ የነበሩ ነዋሪዎች በቀላሉ ንፁህ ውሃ ማግኘታቸው ትልቅ እርካታ ፈጥሯል።
አቶ አወሉ አብዲ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። ከእነዚህ መካከል ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ ህዝባችን ንፁህ ውሃ ሲያገኝ በጤና፣ በትምህርትና በኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ነው ያሉት።
መንግሥታችን የህብረተሰቡን ሕይወት ከመሰረቱ ለመቀየር የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶችን በመንከባከብ መያዝ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡም ሃላፊነት እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የሾቦካ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በዋን ዎሽ ፕሮግራም በጀት የተገነባ ሲሆን፤ ከ40 ሺህ በላይ ለሆነ ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚችል የኦሮሚያ ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

