አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደራችን የኢንዱስትሪ መንደሮች አበርክቷቸው እንዲጎለብት በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል አሉ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዛሬ የከተማችንን ኢኮኖሚ የሚያሳድግና ለበርካታ ዜጎች የተስፋ በር የሚከፍት ታላቅ የምስራች ይዘን ቀርበናል፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግንባታ ስራን በስኬት አጠናቀን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስመርቀናል ብለዋል።
መዲናችን አዲስ አበባ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልማት ከከተማዋ ስትራቴጂካዊ ዕድገት ጋር በማቀናጀት ረገድ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተች ትገኛለች ነው ያሉት።
እየተመዘገቡ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስኬቶች የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከመሰረቱ ከማሻሻል ባለፈ፣ የከተማዋን ገጽታና መልክ በመቀየር፣ ሰፊ የስራ ዕድሎችን በመፍጠርና ማህበረሰባችንን የላቀ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ተኪ የማይገኝለት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያስመዘገቡ እንደሆነ ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደራችን ዋነኛ የኢኮኖሚ ሞተር የሆኑትን እነዚህን የኢንዱስትሪ መንደሮች በማስፋፋት፣ የስራ ቦታዎችን በማዘመንና አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ሀገራዊ አበርክቷቸው እንዲጎለብት በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ ለምረቃ የበቃውና ለታላቅ አገልግሎት ዝግጁ የሆነው የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለዚህ ቁርጠኝነታችን አይነተኛ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት አዲስ መነቃቃትን የሚፈጥር ታላቅ የልማት አሻራችን ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ፣ ጥራትና በጀት ተጠናቆ ለዚህ ታላቅ ስኬት እንዲበቃ ለደከሙ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

