Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ 12 ሺህ የሰላም ሰራዊት አባላት ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2018 ዓ.ም 7ኛ ዙር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ያሰለጠናቸውን 12 ሺህ ምልምል የሰላም ሰራዊት አባላትን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በንድፈ ሐሳብና በወታደራዊ መስክ የሰለጠኑት ተመራቂዎች በከተማዋ እየተከወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ እና ሰላምን ለማጽናት ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።

እስካሁን በመዲናዋ 44 ሺህ ሰልጣኞች ተመርቀው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉን አንስተው÷ በዚህም ትልቅ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።

የዛሬው የምረቃ መርሐ ግብር 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲከናወን ከሚደረጉ ዝግጅቶች መካከል አንዱ መሆኑንም አንስተዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው÷ የሰላም ሰራዊት አባላት ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እየተወጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌ/ጀነራል አስራት ደኔሮ የጸጥታ ሥራ የአንድ ተቋም እና የአንድ አካል ሥራ ባለመሆኑ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

በስልጠናው ውስጥ ያለፉ ተመራቂዎችም ከጸጥታ አካላት ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

በይስማው አደራው

Exit mobile version