Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ዘይቤ ለመቀየርና የምርት ባህልን ለማሳደግ የሌማት ትሩፋት ትልቅ አስተዋጽዖ አለው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ዘይቤ ለመቀየርና የምርት ባህልን ለማሳደግ የሌማት ትሩፋት ትልቅ አስተዋጽዖ አለው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በሐረር ከተማ እየተከናወኑ ያሉትን የማር፣ የወተትና የዶሮ እርባታ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ተዘዋውረን ጎብኝተናል ብለዋል።

የሌማት ትሩፋት የከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ዘይቤ ለመቀየርና የምርት ባህልን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም ገልጸዋል።

በከተማው በኢኒሼቲቩ በግለሰብና በመንግሥት ደረጃ ሼዶችን በመገንባት የማር፣ የወተት፣ የእንቁላልና የዓሳ መንደሮችን የማቋቋም ሥራ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

እንደ ሀገር የአመጋገብ ስርዓታችንን ከመሰረቱ ለመቀየር እና በምግብ እራስን ለመቻል ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ይህ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናልም ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

የእንስሳት፣ የዶሮና ዓሳ ዝርያ ማሻሻልና መኖ ማቀነባበሪያዎች ላይም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

Exit mobile version